"በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት ማንም ማደናቀፍ አይችልም" - ባይደን
አሜሪካ፣ ኳታርና ግብጽ በዶሃ ያረቀቁት የተኩስ አቁም ስምምነት አተገባበር በቀጣይ ቀናት በካይሮ ይመከርበታል ተብሏል
ሃማስ ካልተደመሰሰ ጦርነቱ አይቆምም በሚል አቋሟ የጸናችው እስራኤል የተኩስ አቁም ሃሳቡን ትቀበለዋለች ተብሎ አይጠበቅም
10 ወራት ያስቆጠረውን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት የትኛውም ሀይል ሊያደናቅፈው እንደማይገባ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሳሰቡ።
ፕሬዝዳንቱ ከ40 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት የሚያስቆም ስምምነት ለመፈራረም ተቃርበናል ብለዋል።
ባይደን በስም ባይጠቅሷቸውም የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት የሚያዳክሙ መኖራቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
አሜሪካ፣ ኳታርና ግብጽ ላረቀቁት የተኩስ አቁም ስምምነት ድጋፋቸውን የሰጡት ባይደን፥ ስምምነቱ የመፈረም እድሉ “ተስፋ ሰጪ” መሆኑንም ነው የገለጹት።
በዶሃ ሲካሄድ የቆየው ድርድር በቀጣዩ ሳምንትም ይቀጥላል የተባለ ሲሆን፥ በስምምነቱ አተገባበር ዙሪያ ከፍተኛ ባለስልጣኖች በካይሮ እንደሚመክሩበትም ተጠቁሟል።
የእስራኤል አጋር የሆነችው አሜሪካ የጋዛው ጦርነት ቀጠናዊ መልክ እንዳይዝ ስምምነቱ በፍጥነት እንዲፈረም ጫና እያደረገች መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
ባይደን በግንቦት ወር መጨረሻ ያቀረቡት በሶስት ምዕራፍ ተግባራዊ የሚደረግ የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ተከታታይ ውይይት ቢደረግበትም እስካሁን ስምምነት ላይ ሳይደረስበት መቅረቱ የሚታወስ ነው።
እስራኤል በቴህራን የሃማስ የፖለቲካ መሪውን ኢስማኤል ሃኒየህ መግደሏ ከተነገረ በኋላ ቀጠናዊ ውጥረቱ መባባሱን ተከትሎም ዋይትሃውስ የተኩስ አቁም ስምምነት በፍጥነት እንዲደረስ እየወተወተች ነው ተብሏል።
ባይደን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን አንቶኒ ብሊንከን ወደ እስራኤል በመላክ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን እንደሚያግባቡም ነው የተገለጸው።
ከቴህራን ሊቃጣ ለሚችል ጥቃት ራሷን ዝግጁ ማድረጓን የቀጠለችው ቴል አቪቭ ሃማስ ካልተደመሰሰ ጦርነቱ አይቆምም የሚለውን አቋሟን ለውጣ የተኩስ አቁም ስምምነት ትፈራረማለች ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።
ሃማስም ዘላቂና የእስራኤል ጦርን ከጋዛ የሚያስወጣ ስምምነት እንጂ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንደማይፈርም ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።
የቴህራን እና ቴል አቪቭ ውጥረት መጋጋል ግን ሁለቱንም ሃይሎች ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይጠበቃል።
ኢራን የቀጠናው ባላንጣዋ እስራኤል በጋዛ ተኩስ ለማቆም ከተስማማች በሃኒየህ ግድያ ምክንያት ልትሰነዝረው ያሰበችውን የአጻፋ እርምጃ ከመፈጸም እንደምትታቀብ መግለጿ አይዘነጋም።