የ14 አመቱ ትውልደ ኢትዮጵያ “የአሜሪካ ወጣቱ ምርጥ ተመራማሪ” ተብሎ ተሸለመ
ሄማን በቀለ የተሰኘው ታዳጊ የቆዳ ካንሰርን የሚከላከል ሳሙና በመስራት 25 ሺህ ዶላር የሚያሸልም ውድድርን አሸንፏል
ታዳጊው በርካሽ ለገበያ ይቀርባል ያለውን ሳሙና ለታዳጊ ሀገራት በነጻ ለማከፋፈል አቅዷል
የ14 አመቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ታዳጊ ሄማን በቀለ “የአሜሪካ ወጣት ምርጥ ተመራማሪ” ክብርን ተቀዳጀ።
የቆዳ ካንሰርን የሚከላከል ሳሙናን ይዞ በመቅረብ ከ9 ተወዳዳሪዎች ጋር የተፎካከረው ሄመን አሸናፊ ሆኗል።
በዚህም የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት ተበርክቶለታል።
በ4 አመቱ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የተጓዘው ሄማን የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በርካሽ ለገበያ የሚውል የካንሰር መከላከያ ሳሙናን ነው ያስተዋወቀው።
“የቆዳ ካንሰር በአብዛኛው በታዳጊ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ላይ ነው የሚከሰተው” የሚለው ታዳጊው፥ በ0 ነጥብ 05 ዶላር ለገበያ የሚውሉ ሳሙናዎችን ሰርቷል።
“በቀላሉ ልንከላከላቸውን የምንችላቸው በሽታዎች ከቆይታ በኋላ እስከ 40 ሺህ ዶላር ሊያስወጡን ይችላሉ” በማለትም የቆዳ ካንሰርን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ያብራራል።
ታዳጊው ሳሊሳይክሊክ አሲድ፣ ግላይኮሊክ እና ትሪቲንይን የተሰኙ የቆዳን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያሳድጉ ነገሮች ከሳሙና መስሪያ ግብአቶች ጋር በመቀላቀል ነው የቆዳ ካንሰርን ከመባባሱ በፊት ለመቆጣጠር ያግዛል የተባለውን ሳሙና የሰራው።
ሄማን በቀለ የተሸለመውን 25 ሺህ ዶላር የፈጠራ ስራውን በስሙ ለማስመዝገብና ወደ ኮሌጅ ሲገባ ምርምሩን ለመቀጠል እንደሚጠቀምበት ገልጿል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ታዳጊ በ2028 የሳሙና ምርቶቹን በታዳጊ ሀገራት በነጻ የሚያከፋፍል ግብረሰናይ ድርጅት ለማቋቋም ማቀዱን መግለጹን ኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል።