ህጻናትን ከግጭት እና ጦርነት ዜናዎች ስነልቦናዊ ተጽእኖ እንዴት እንጠብቅ?
ዩኒሴፍ የህጻናትን የጦርነት እና ግጭቶች አረዳድ እንዲሁም የመረጃ ተጋላጭነት ወላጆች ሊከታተሉ እንደሚገባ አሳስቧል
የግጭት እና ጦርነት መረጃዎች በተደጋጋሚ በሚነገርባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህጻናት ለጭንቀት፣ ፍርሀት እና ድብርት ሊጋለጡ ይችላሉ ተብሏል
ምደራችን የጦርነት ዜና ወሯታል፤ ሰላም የሆነ የአለም ክፍል የሌለ እስኪመስል የግጭት ዜናዎች ፈጥነው ከጆሮ እና ከአይናችን ይደርሳሉ፡፡
የሚደርሱንን መረጃዎች ተከትሎ የምንሰጣቸው ምላሾች እንዲሁም ከሰዎች ጋር የምናደርገው ውይይት መረጃዎቹ በቀጥታ በማይደርሳቸው በአካባቢያችን በሚገኙ ህጻናት ላይ ከፍተኛ ስነ ልቦናዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው ስንቶቻችን እናውቃለን?
የጦርነት ክፋቱ በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸው ንጹሀን ላይ ቀድሞ በትሩን ማሳረፉ ነው፡፡
በግጭት ቀጠና ውስጥ ከሚኖሩት፣ ሞት እና ግዳያን ከሚመለከቱ፣ በልጅ እግራቸው ከሞት ለማምለጥ ከሚሮጡት ተሻግሮ ከግጭቱ በብዙ ርቀት ላይ የሚገኙ ህጻናት የአዕምሮ ጤናንም ይጎዳል፡፡
ዩኒሴፍ ግጭት እና ጦርነት መረጃዎች ወይም ዜናዎች በተደጋጋሚ በሚነገርባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህጻናት ለጭንቀት፣ ፍርሀት እና ድብርት ሊጋለጡ ይችላሉ ብሏል፡፡ በተጨማሪም ቁጠኛ እና ተነጫናጭ ባህሪንም እንደሚላበሱ ነው ያመላከተው፡፡
ስለሆነም ወላጆች ልጆቻቸው ለነዚህ መረጃዎች ያላቸውን ተጋላጭነት በመከታተል ተከታዮቹን መፍትሄዎች ቢከተሉ ሲል ምክረ ሀሳቦችን ዘርዝሯል፡፡
1. ወላጆች ልጆቻቸው በአካባቢያቸው ስላለ ጦርነት ምን ያክል እንደሚያውቁ መጠየቅ
መሰል መረጃዎችን ልጆች ከየትኛውም አጋጣሚ ሊሰሟቸው እንደሚችል በማሰብ ወላጆች ልጆቻቸቸውን ስለሚያውቁት ነገር በመላ መጠየቅ፤ ከዛም በአዕምሯቸው የያዙት መረጃ ምን ድረስ እንደሆነ በመረዳት አስተሳሰባቸውን መቃኝት እና በጣም መጥፎ የተባሉ የጥላቻ እና የቂም የሚመስሉ ሀሳቦች ካሉ እንዲተውት ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡
2. በእድሜያቸው ልክ ማወቅ የሚገባቸውን ብቻ እንዲያውቁ መከታተል
በዘመነ ዲጂታላይዜሽን የመረጃዎችን ፍሰት መገደብ የማይቻል ነው ያለው ዩኒሴፍ፥ ህጻናት በሚያውቁት መረጃ ልክ ተጽእኖ ስር እንዳይወድቁ የሰሙት እና ያዩት ለባህርያቸው ለውጥ ምክንያት እንዳይሆን ለመሰል መረጃዎች ያላቸውን ተጋላጭነት መከላከል እንደሚገባ ይመክራል።
ከሰዎች ጋር በሚኖር ውይይት ስለምንሰነዝራቸው ሀሳቦችም ሆነ በተለያዩ መገናኛ መንገዶች የሚሰራጩ የጦርነት ዜናዎችን እንዳይመለከቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል፡ም ብሏል።
3. ከአሰቃቂ ንግግሮች ራስን መቆጠብ
የሰዎችን አሟሟት አይነት፣ የግጭት ሂደቶችን ህጻናት ባሉበት ከመናገር መቆጠብ፣ ወላጆች በአካባቢያቸው እና ከእነርሱ ሩቅ በሚካሄዱ ግጭት እና ጦርነቶች ላይ የትኛውም አይነት ወግንና ቢኖራቸው ይህንን ከማንጸባረቅ ሊታቀቡ ይገባል፡፡
ይህም ህጻናት የወላጆቻቸቸውን ድጋፍ እንዲሁም ነቀፌታ ይዘው ሄደው ከእኩዮቻቸው ጋር እንዳይጋጩ ንጹህ ለጋ አዕምሯቸውን ይዘው እንዲያድጉ የሚያግዝ ነው፡፡
በተጨማሪም ፍርሀት እና ስጋት እንዳያድርባቸው ከአቅማቸው በላይ ስለጉዳዩ እንዳያሰላስሉ እንዳይጨነቁም ያግዛቸዋል፡፡
4. መልካም ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ እና ልጆችን መከታተል
ህጻናት ስለጦርነት መረጃ እንዳላቸው ካረጋገገጥን በዚህ ውስጥ ስለሚከናወኑ መልካም ነገሮች እንዲያውቁ ማድረግ፡፡
ሰዎችን ለመርዳት የሚደረግ ጥረት፣ ስለ ሰላም እና እርቅ እንዲሁም ስለጦርነት መቆም የሚያነሳሱ አብነት የሆኑ ግለሰቦችን እንዲያውቁ ማገዝ፣ በተቃራኒው የግጭትን አስከፊነት በልኩ እንዲረዱ ማስቻል ይጠበቃል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ህጻናት አይረዱም አልያም እምብዛም አይገነዘቡትም በሚል የመረጃ ተጋላጭነታቸውን ችላ አለማለት ይገባል ብሏል ዩኒሴፍ።