የጦርነት ምንዱባን ህጻናትን ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ የሰነቀችው ራሄል ገ/እግዚሀብሄር
በሰሜኑ ጦርነት ተጽዕኖ ለደረሰባቸው ህጻናት “ርሻን” የተሰኘች የህጻናት መጽሀፍ ታተመች
84 ገጾች ያሏት ርሻን መጽሀፍ ልጆችን የሚጎተጉቱ ታሪኮችን በመያዝ በትግራይ ለሚገኙ ህጻናት እየደረሰች ነው
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ጠባሳ ያረፈባቸውን ህጻናት “ወደ መደበኛ” ህይወት መመለስ ያለመችው “ርሻን” የህጻናት መጽሀፍ ታትማለች።
ከትምህርት ቤት ደጆች የራቁት ህጻናት ባልበሰለ አእምሯቸው የታተሙባቸውን ጠባሳዎች ለማረቅ በሚል ርሻን መጽሀፍ በትግርኛ ተጽፋለች።
በ84 ገጾች ልጆችን “የሚጎተጉቱ ታሪኮችን” የያዘች መጽሀፏ በቀጥታ በትግራይ ለሚገኙ ህጻናት እየደረሰች ነው።
የጦርነት ዳፋ በህጻናት ላይ እምብዛም ትኩረት አለማግኘቱን የምትናገረው የርሻን ጸሀፊ ራሄል ገ/እግዚሀብሄር፤ በሰሜኑ ጦርነት የህጻናት ቀጥተኛ ተጎጂነት ሲያሳስባት እንደነበር ትናገራለች።
ጥቅምት 23 የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ወደ መቀሌ ያቀናችው የርሻን መጽሀፍ ደራሲ፤ በጉዞዋ የታዘበችው ሁነት የልጆች መጽሀፍ ለመጻፍ ገፍቷታል።
“መጠለያ ጣቢያ ያሉትን፣ ከተማ ላይ ያሉትንም ልጆች ለማናገር ሞክሬ ነበር። ሙሉ ለሙሉ አእምሯቸው ላይ ያለው ከጦርነቱ ጋር የተያያዘ ነው። ጨዋታቸው የጦርነት ጨዋታ ነው። በሆነ ነገር ሽጉጥ ሰርተው፤ ወታደራዊ ሰልፍ እያደረጉ ነው የሚጫወተቱት።
ጭንቅላታቸው ላይ አልጠፋም። አውሮፕላን ሲመጣ ጥቃት የሚያደርስ ነው የሚመስላቸው። እኛ ልጅ ሆነን ምኞት ነበረን። ምን መሆን ትፈልጋላችሁ? ስንባል ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ፣ ፓይለት መሆን እፈልጋለሁ ነው የምንለው። እነሱ [ህጻናቱ] ምኞታቸውን ስጠይቃቸው ከጦርነቱ ጋር የተያያዘነው። ‘እኔ ተዋጊ፣ ወታደር መሆን ነው የምፈልገው፣ ሽጉጥ እንዲኖረኝ ነው የምፈልገው፣ ታንክ መንዳት ነው የምፈልገው’ በቃ ይሄ ነው ምኞታቸው” ትላለች።
ይህም ለርሻን ጥንስስ መሰረት ጣለ። በትግራይ ቆይታዋ ራሄል አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ በማለት ማሰላሰል እንደጀመረች ለአል ዐይን ተናግራለች።
በሙያዋ ጋዜጠኛ የሆነችው ራሄል ገ/እግዚሀብሄር፤ “ከጦርነት ውጭ ሌላ ህይወት” እንዳለ ለማሳየት መጽሀፍ መጻፍን ጥሩ መንገድ አድርጋ መውሰዷን ትናገራለች።
ህጻናት መንፈሳቸው እንዲነሳሳ የቅዱስ ያሬድ፣ የዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖምና የሌሎችም ታዋቂ ሰዎች እውነተኛ ታሪኮችንና የፈጠራ ታሪኮችን በአጠቃላይ አምስት ታሪኮችን የሰነደችው ርሻን መጽሀፍ ባለፈው ሚያዚያ ወር ታትማ በመጠለያ ጣቢያዎችና በት/ቤቶች ተሰራጭታለች።
ጸሀፊዋ “የሚያነሳሱ፣ የሚያበረታቱ፣ መልካም ማድረግን፣ ሀገርን፣ ባህልንና ታሪካቸውን እንዲያውቁ የሚያደርጉ ጽሁፎች ናቸው” በማለት ስለ መጽሀፉ ይዘት ገልጻለች።
ርሻን መጽሀፍ በነጻ ለህጻናት ተደራሽ እንድትሆን ማህበራዊ የትስስር ገጾችን በመጠቀም ሰዎች በቀጥታ ገዝተው “የመጽሀፍ ልገሳ” በማድረግ ተደራሽ መሆለኗን ራሄል ገ/እግዚሀብሄር ተናግራለች።
አንድ ሽህ መጻህፍትን በማሳተም 300 እትም ተፈናቅለው ላሉ ህጻናት፤ 500 እትም ደግሞ በትግራይ ትምህርት ቢሮ በኩል ለተማሪዎችና ለት/ቤቶች እንዲደርስ ማድረጓን ገልጻለች።
ራሄል ገ/እግዚሀብሄር ህጻናት ከጦርነት ድጥ እንዲወጡ ለመጎትጎትና ትምህርት እስኪጀመሩ ድረስ የማንበብ ዝንባሌያቸውን ለማምጣት የጻፈችውን መጽሀፍ በሰፊው ተደራሽ ማድረግን ወጥናለች። ለዚህ ውጥኗ የሚረዷትን ደጋፊዎችና ለጋሾችን ትሻለች።