የሃንጋሪ ጠ/ሚኒስትር ሀገራቸው ከሕብረቱ አትወጣም ብለው ነበር
27 ሀገራትን በአባልነትን ያቀፈው የአውሮፓ ሕብረት ፖለቲካዊ ያሆኑ ጉዳዮችን ፖለቲካዊ ማድረጉ እንዲዳከም አድርጎታል ስትል ቡዳፔስት ገለጸች፡፡
ከሩሲያ ቱዴይ (አርቲ) ጋር ቆይታ ያደረጉት የሃንጋሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፒተር ሲጃርቶ የአውሮፓ ሕብረት የኮሮና ወረርሽኝን፣የኢኮኖሚ ውድቀትንና የአውሮፓ የኃይል ቀውስን በተመለከተ ሀገራቸው እና ሩሲያ ጋር መስራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የብራሰልሱ ተቋም ዛሬ በሚጠናቀቀው 2021 ተዳክሞ እንደነበርም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ህብረቱ በርካታ ጉዳዮችን አላግባብ ፖለቲካዊ እንዳደረጋቸውም የሃንጋሪው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንስተዋል፡፡
የኮሮና ክትባትን እና የኃይል አጠቃቀምን አላግባብ ፖቲካዊ ማድረግ እንደማያስፈልግም የህብረቱ አባል የሆነችው ሃንጋሪ ጠቅሳለች፡፡
ቡዳፔስት በሩሲያ ተመራማሪዎች የተዘጋጀውን ስፑትኒክ ክትባትን ለመጠቀም ስትራቴጂያዊ ውሳኔ ማሳለፏን አስታውቀዋል፡፡ ሃንጋሪ ክትባቱን ለመጠቀም የወሰነችው አባል የሆነችበት የአውሮፓ ሕብረት ሳያጸድቀው እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡ አሁን ላይ የአውሮፓ የመድሃት ኤጄንሲም ስፑትኒክ የተባለውን የሩሲያን የኮሮና ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ያጸድቃል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
የሃንጋሪው ሚኒስትር “የሩሲያ እና የአሜሪካ ቀጥተኛና ቀጣይነት ያለው ውይይት ለእኛ በምዕራብ አውሮፓ ለምንገኘው ሀገሮች እጅግ ጠቃሚ ነው” ያሉ ሲሆን የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በአዲሱ የፈረንሆች ዓመት ሊገኛኙ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡
ከአራት ሳምንታት በፊት በበይነ መረብ ውይይት ያደረጉት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን በድጋሚ ሊወያዩ እንደሚችሉም እየተጠበቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሃንጋሪ አባል ከሆነችበት የአውሮፓ ሕብረት ጋር በስደተኞች ጉዳይ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባቷ ይታወሳል፡፡ የህንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ሃንጋሩ የአውሮፓ ሕብረት እንዲሻሻል ታደርጋለች እንጅ ሕብረቱን ለቃ አትዋም ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በርካታ የሃንጋሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አውሮፓ ጸረ ሃንጋሪ የሆነ አቋም አለው የሚል ሃሳብም አቅርበው ነበር፡፡
የአውሮፓ ሕብረት እና የሃንጋሪ ፍጥጫና መካረር ቡዳፔስትን እንደ ለንደን ከሕብረቱ ያስወጣት ይሆን የሚለው አሁንም እያነጋገረ ነው፡፡