ምክክሩ በመጪው ጥር በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ይካሄዳል ተብሏል
በዩክሬን ጉዳይ ፍጥጫ ውስጥ የገቡት አሜሪካ እና ሩሲያ ውጥረት ውስጥ በከተታቸው ጉዳይ ላይ ሊመክሩ ነው፡፡
ምክክሩ በመጪው በፈረንጆቹ ጥር 10 በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እንደሚካሄድ ተነግሯል፡፡
ሞስኮው በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ አንድ መቶ ሺ ገደማ ጦሯን ማስጠጋቷን ተከትሎ ወረራ ልትፈጽም ነው በሚል ከምዕራባውያን ጋር ስትወዛገብ ነበረ፡፡
ምዕራባውያን እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በዩክሬን በኩል ጦራቸውን እያስጠጉ ነው ያለችው ሩሲያ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቃለች፡፡
አባላቸው ያልሆነችውን ዩክሬንን አለንልሽ ከማለትና በጦር መሳሪያ ከመደገፍ እንዲታቀቡም ነበር ስታስጠነቅቅ የነበረችው፡፡
ኔቶ የሶቪዬት ህብረት አካል የነበሩ ሃገራትን በአባልነት ለመያዝ እና በሃገራቱ የጦር ሰፈሮችን ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያቆምና ምስራቅ አውሮፓን ለቆ እንዲወጡ ሩሲያ ቀደም ሲልም አስጠንቅቃ ነበር፡፡
ሞስኮ ልክ እንደ ክሬሚያ ሁሉ ተጨማሪ የዩክሬን ግዛቶችን በወረራ ልትይዝ አስባለች ያሉ ምዕራባውያንም በማዕቀብ ጭምር ሲስፈራሩ ነበር፡፡
በዚሁ ምክንያት የነገሰውን ውጥረት ለማርገብም ነው በጄኔቭ እንመክራለን ያሉት እንደ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ገለጻ፡፡
የጄኔቩን ቀጥሎ ሞስኮው ከኔቶ እና ከአውሮፓ የጸጥታ ትብብር ድርጅት ጋር እንደምትመክር ተገልጿል፡፡
ምክክሩ ቢደረግም አሁንም ጫና ማድረጓን እንደማታቆም አሜሪካ አስታውቃለች፡፡
በሜዲትራኒያን ባህር ላይ የሚገኙ የጦር መርከቦቿ ወደ መካከለኛው ምስራቅ መጓዛቸውን ትተው በዚያው እንዲቆዩም አዛለች፡፡