በአፍሪካ በአደገኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኝው ሕገ ወጥ የሰውነት ክፍሎች ሽያጭ
ከአፍሪካ ተነስቶ ወደ ሌሎች የአለም ክፍሎች የሚደረገው ህገ ወጥ የአካል ክፍሎች ሽያጭ በአመት ከ 1 ቢሊየን ዶላር ባለይ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ነው
በአሁኑ ወቅት አንድ ኩላሊት እስከ 150 ሺህ ዶላር ድረስ በጥቁር ገበያ እየተሸጠ ይገኛል
በአፍሪካ ሀገራት ህገወጥ የሰውነት አካላት ሽያጭ እና ዝውውር በወረርሽኝ ደረጃ በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተነገረ፡፡
ኩላሊት እና ልብን የመሳሰሉ የሰው ልጅ የውስጥ አካላት በፍቃደኝነት ለገበያ ከሚቀርቡት ሁኔታ ጀምሮ፤ ሰውን በመግደል እና በሆስፒታሎች አካባቢ በሚሰራው ህገወጥ ተግባር የሚደረገው ግብይት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል ነው የተባለው፡፡
በአፍሪካ የሚገኝው የድህነት ደረጃ እንዲሁም ስራ አጥነት ሰዎች የሰውነት አካላቸውን እንዲሸጡ እያሰገደደ እንደሆነ ሲነገር፤ በሆስፒታል ውስጥ በቀዶ ጥገና ጊዜ እና ከሞቱ ሰዎች የሚሰረቁ የሰውነት ክፍሎች በአውሮፓ እና አሜሪካ ገበያ እየተቸበቸቡ እንደሚገኙ የዶቼቬለ ዘገባ ያሳያል፡፡
ይህ የሰውነት ክፍሎች ሽያጭ እና ህገወጥ ዝውውር በአመት ከ840 ሚሊየን እስከ 1.7 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ እንደሚንቀሳቀስበት ነው የተገለጸው፡፡
በመላው አፍሪካ የሰውነት ክፍልን መሸጥ የተከለከለ ቢሆንም በ2022 በኬንያ የሚገኝው የኬንያታ ሆስፒታል በፌስቡክ ገጹ “ለኩላሊቴ ስንት ትከፍሉኛላቸሁ” የሚሉ መልዕክቶች በተደጋጋሚ እየደረሰው መሆኑን ተከትሎ ኩላሊት እንገዛም የሚል መልዕክት በገጹ ላይ ለመለጠፍ ተገዷል፡፡
ምዕራብ ኬንያ ከፍተኛ የሰው ልጅ አካላት ሽያጭ ከደራባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ሲሆን በደላሎች እና በህክምና ባለሙያዎች አስማሚነት በሚደረገው ድርድር መሰረት ለአንድ ኩላሊት እስከ 6 ሺህ ዶላር ድርስ ይከፈላል፡፡
የአውሮፓ ፓርላማ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ደላሎች ኩላቲቱን ለገበያ የሚያቀርቡበት ዋጋ እስከ 150 ሺህ ዶላር ድረስ እንደሚደርስ የሚያመለክት ነው፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የአደገኛ እጽ እና ወንጀል ቢሮ በበኩሉ ከደሀ ሀገራት ወደ ሀብታሞቹ ሀገራት የሚደረገው ህገወጥ የሰውነት ክፍሎች ዝውውር መቆጣጠር በሚያስቸግር ሁኔታ እየተስፋፋ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች አካላቸውን ለመሸጥ ሁለቴ እንደማያስቡ ከዛ በኋላም በጤናቸው ላይ ስለሚደርስባቸው ነገር እምብዛም እንደማይጨነቁ የሚያትተው ዘገባው ሆዳቸው አካባቢ የቀዶ ጥገና ጠበሳ ያለባቸው ወጣቶችን መመልከት እየተለመደ መጥቷል ነው ያለው፡፡
ይህንንም ተከትሎ የሰውነት አካላት ሽያጭን የሚያጧጡፉ ጥቁር ገበያዎች በመላው አፍሪካ በወረርሽኝ ደረጃ እየተስፋፉ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
ግበጽ ፣ ኬንያ ፣ ሊቢያ ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄርያ ይህ ችግር በአስከፊ ሁኔታ ከሚገኝባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይገኛሉ፡፡
የህገወጥ ዝውውር መስመሩ እጅግ የተወሳሰበ አለም አቀፍ የጤና ተቋማትን ፣ ሀኪሞችን፣ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖችን እና የመንግስት ባለስልጣናትን ጭምር የሚያሳትፍ ነው ተብሏል፡፡
ድርጊቱ ህገ ወጥ መሆኑን ተከትሎ አካላቸውን ለመሸጥ የተስማሙ ሰዎች ቀዶ ጥገናውን የሚያከናውኑት ንጽህናው ባልተጠበቀ ፣ የህክምና መሳርያዎች ባልተሟሉባቸው ድብቅ ስፍራዎች በመሆኑ ልገሳውን ካደረጉ በጥቂት ጊዜያት ህይወታቸው የሚያልፉ ሰዎቸ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
እንደ አለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ በአሁኑ ወቅት በመላ አህጉሪቷ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት 35 ብቻ ናቸው፡፡