በአዲስ አበባ ባለፉት 2 ቀናት ብቻ በደረሱ ድንገተኛ አደጋዎች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል ተባለ
ባለፉት ስድስት ወራት በከተማዋ በደረሱ መሰል አደጋዎች የ62 ሰዎች ህይወት አልፏል
ከጥምቀት በዓል ጋር የማይገናኙ ሶስት አደጋዎች በነዚሁ ቀናት ውስጥ ማጋጠማቸውም ተነግሯል
በአዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ቀናት በደረሱ አደጋዎች ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተገለጸ ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንደገለጸው ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ሶስት የእሳት አደጋዎች ደርሰዋል፡፡
በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ለአል ዐይን እንዳሉት ባለፉት ሁለት ቀናት በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ ሶስት የእሳት አደጋዎች ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡
የመጀመሪያው አደጋ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ፈረንሳይ ብረት ድልድይ አካባቢ በመኖሪያ ቤት ላይ የደረሰ ሲሆን 50 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡
ሁለተኛው እና ከባዱ አደጋ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ልዩ ስሙ አባኮራን ኢንዱስትሪ መንደር ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን አቶ ንጋቱ አክለዋል፡፡
በአካባቢው ያለው መንገድ ለተሽከርካሪ አመቺ አለመሆኑ አደጋውን በፍጥነት እንዳንቆጣጠር እና ብዙ ግምት ያለው ንብረት እንዲወድም ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት ባለሙያው፡፡
የቢሮ እቃዎችን እና የተለያዩ የእደ ጥበብ ውጤቶች ይሰራበት የነበረው ይህ የኢንዱስትሪ መንደር ከሁለት ወር በፊት ተመሳሳይ አደጋ ደርሶበት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ሶስተኛው አደጋ ትናንት ሃሙስ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ/ም በቦሌ ክፍለ ከተማ አትላስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጀርባ የደረሰ ሲሆን በአደጋው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ዋጋ ያላቸው ሰባት ሼዶች መቃጠላቸውን አቶ ንጋቱ ገልጸዋል፡፡
የአደጋዎቹ መንስኤ በመጣራት ላይ ነው ያሉት አቶ ንጋቱ የኮሚሽኑ አደጋ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች እና የሌሎች ተቋማት ድጋፍ ባይደረግ ኖሮ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት ሊወድም ይችል እንደነበር አቶ ንጋቱ አክለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 236 አደጋዎች ተከስተው የ62 ሰዎች ህይወት ማለፉንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ከተከሰቱት አደጋዎች ውስጥ 136 የእሳት ቃጠሎ ሲሆኑ 100 አደጋዎች ደግሞ ከእሳት ውጪ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ናቸው፡፡
ከተከሰቱት አደጋዎች 218 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ የተከሰቱ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ናቸው ተብሏል፡፡
የ62 ሰዎች ህይወት ባለፈበት በነዚህ አደጋዎች 112 ሰው ደግሞ ሲቆስሉ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ጥረት ደግሞ የ51 ሰዎችን ህይወት ማዳን መቻሉን ተቋሙ አስታውቋል፡፡