በአዲስ አበባ በገና ዋዜማ እና በዓሉ ዕለት አራት አደጋዎች ተከስተዋል
በአራቱ አደጋዎች የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ 300 ሺህ የሚገመት ንብረት ወድሟል ተብሏል
ሰራተኞች ባደረጉት ጥረትም ስምንት ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ከውድመት ታድገዋል ተበሏል
በአዲስ አበባ በገና በዓል ዋዜማ እና በዓሉ ዕለት አራት አደጋዎች ደርሰው የሰው ህይወት እና ንብረቶች መውደማቸውን የከተማው እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገልጿል፡፡
በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ንጋቱ ማሞ ለአልዓይን እንዳሉት በገና ዋዜማ እና በዓሉ ዕለት አራት አደጋዎች ደርሰው 290 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ንብረቶች ወድመዋል ብለዋል፡፡
የመጀመሪያው አደጋ የደረሰው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ሲሆን ልዩ ቦታው አዲሱ ሰፈር በሚባል ቦታ ሬስቶራንት ውስጥ የደረሰ አደጋ ነው፡፡በዚህ አደጋ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
ሌላኛው አደጋ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ጎርደሜ ወንዝ ውስጥ አስከሬን መታየቱን ተከትሎ በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት ወደ ስፍራው ባለሙያዎች አቅንተው አስከሬኑን እንዳወጡ አቶ ንጋቱ ነግረውናል፡፡
በወንዙ ውስጥ የተገኘው አስከሬን የቆየ አስከሬን መሆኑን ተከትሎ ለፖሊስ ማስረከባቸውንም አቶ ንጋቱ ገልጸዋል፡፡
ሶስተኛው አደጋ የደረሰው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቀላል የእሳት አደጋ መድረሱን የተናገሩት አቶ ንጋቱ የወደመውም ንብረት አነስተኛ መሆኑን አክለዋል፡፡
አራተኛው አደጋ የተከሰተው በኮልፉ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ጫረታ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በደረሰ የእሳት አደጋ ሶስቱ ሱቆች መቃጠላቸው ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በከተማዋ አራት ቦታዎች በደረሱ አደጋዎች 290 ሺህ የሚገመት ንብረት መውደሙን የተናገሩት አቶ ንጋቱ የተቋሙ ሰራተኞች ባደረጉት ጥረትም 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ከውድመት መታደጋቸውንም ገልጸዋል፡፤
ህብረተሰቡ እራሱን ከአደጋዎች ከመጠበቅ አንጻር እና የጥንቃቄ እርምጃ አስተሳሰቡ እየጨመረ በመምጣቱ አደጋዎች እንዲቀንሱ ማስቻሉንም አቶ ንጋቱ ተናግረዋል፡፡