የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑን ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ አስታወቁ
የአህጉረቱ መሪዎች ተስማምተው የህብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸውም ምስጋና አቅርበዋል
በኮሮና ምክንየት ተቋርጦ የነበረው ጉባዔው ከሶስት ዓመታት በኋላ ነው ዳግም በአዲስ አበባ የሚካሄደው
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
“የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ተስማምተው የኅብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።
የኮሮናን መስፋፋ እና ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታን እንደ ምክንያት በማሳት የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በነበሩ አካላት ኢትዮጵያ አዝና እንደነበረም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በዓመት ሁለት ጊዜ ኪደረጉት የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ መካከል በኮሮና ምክንየት ተቋርጦ የነበረው የመጀመሪያው ጉባዔ ከሶስት ዓመታት በኋላ ዳግም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጋር በመሆን መንግስት ልዩ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱንም ገልፀዋል።
“ኢትዮጵያ - የአፍሪካዊነትን ጉዳይ እንደ መጀመሪያ አጀንዳዋ እንጂ እንደ ሁለተኛ አድርጋ ወስዳው እንደማታውቅ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዚህ ዘመን መሪዎችም ይህንን ተገንዝበው አጋርነታቸውን በሚያሳይ መልኩ የኅብረቱን ጉባኤ በአካል እዚህ ለማከናወን ያሳለፉትን ውሳኔ ኢትዮጵያ ታደንቃለች” ብለዋል።
“ጉባኤው እዚህ መካሄዱ የሚኖረውን ትርጉም የተገነዘቡና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም፣ ለአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እና የአፍሪካ ጉዳዮች በአፍሪካውያን እንዲታዩ ያላትን የጸና መርሕ ከፍ ያለ ዋጋ የሰጡ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱን መርጠዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ደስ ተሰኝታለች” ሲሉም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያውያን ባስተላፉት መልእክትም፤ “አሁን ጉባኤውን ለማከናወን የቀረን ሁለት ሳምንት ብቻ ነው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገን ጉባኤውን ማሳካት አለብን፤ የጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄድ ትርጉሙ ብዙ ነው። ሰላማችንና ደኅነታችንን የምናስመሰክርበት፣ ለአፍሪካ ጉዳዮች ያለንን አቋም በድጋሚ የምናስመሰክርበት፤ የኢትዮጵያን መልካም ሁኔታ ለአፍሪካውያን ወገኖቻችን በተግባር የምናሳይበት፤ ከዚህም አልፎ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የምናገኝበት ጉባኤ ነው። እናም ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ከሁላችንም ብዙ ይጠበቃል” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
የጸጥታ አካላት፣ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች፣ እንዲሁም የመዝናኛና ቱሪዝም ሥፍራዎች ከእናንተ ብርቱ ዝግጅት እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።