በየአመቱ ህዳር 23 የሚከበረውን የአካል ጉዳተኞች ቀን በኢትዮጵያ ደረጃ በሻሸመኔ ከተማ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
በዋዜማው በሻሸመኔ በነበረው ዝግጅት በአካል ጉዳተኞች የተለያዩ ተግዳሮቶች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በአካል ጉዳተኞች የተሰሩ የተለያዩ የዕደ ጥበብ ስራዎችም ዓውደርዕይም ተካሂዷል የኢቢሲ መረጃ እንደሚያመለክተው፡፡
በዝግጅቱ ላይ የዘርፉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የተለያዩ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡
ከ100 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ህዝብ እስከ 20 ሚሊዮን የሚሆነው የተለያየ አይነት የአካል ጉዳት ያለው እንደሆነ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁንና በሀገሪቱ የሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎችም ሆኑ ውሳኔዎች እምብዛም አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግስት ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ትኩረት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ጊዜያት በራሳቸው ተነሳሽነት ለአካል ጉዳተኞች የተለያዩ ስጦታዎችን ማበርከታቸውም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡