ኢንተርኔት ዳግም በተለቀቀባቸው የአማራ ክልል ከተሞች ያለው የአገልግሎት ሽፋን ምን ይመስላል?
በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት መለቀቁን ተጠቃሚዎች ተናገሩ
ነዋሪዎች በዚህ ዘመን ከኢንተርኔት አገልግሎት ውጭ መሆን ከብዙ ነገር ወደ ኋላ እንድንቀር አድርጎናል ይላሉ
ከ11 ወራት በላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦባቸው በነበሩ የአማራ ክልል የተወሰኑ ከተሞች አገልግሎት ድጋሚ መጀመሩን ተጠቃሚዎች ተናግረዋል፡፡
በመንግስት እና በአማራ ክልል በሚገኙ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውግያ መቀስቀሱን ተከትሎ ከባለፈው አመት ሀምሌ ወር ጀምሮ በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች አገልግሎቱ በመቋረጡ የተነሳ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
በእነዚህ ከተሞች የኢንተርኔት መቋረጥ የፈጠረው ጫና ምንድን ነው?
የኢንተርኔት መቋረጥ በባንክ አገልግሎት፣ በንግድ ስራ፣ በግብረ ሰናይ ተቋማት እንቅስቃሴ እና በዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ አልአይን አማረኛ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ያሰባሰበው መረጃ አመላክቷል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪው ይናገር አለሙ “በዚህኛው ዘመን ኢንተርኔት ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ከመሆኑ ባለፈ ለስራ እና ለህይወትህ የሚጠቅሙ ጉዳዮችን የምትከታተልበት መንገድ ነው ከዚህ አገልግሎት ለ12 ወራት ያህል መታገድ ማለት ወደ ኋላ እንደመመለስ ነው” ሲል ይናገራል፡፡
ሌላኛው የባህርዳር ከተማ ነዋሪ አቤል አዲሱ በበኩሉ ኢንተርኔት ከመዝናኛነት ያለፈ ጥቅም በሚሰጥበት በዚህ ጊዜ የአገልግሎቱ መቋረጥ በበርካታ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ኑሮ ላይ ተጽእኖው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጿል፡፡
“ጦርነቱ በተጀመረበት አካባቢ የውጭ የትምህርት እድል አግኝቼ ሂደቱን ለመጨረስ በመጻጻፍ ላይ ነበርኩኝ ሆኖም ውግያው ሲፋፋም እና ኢንተርኔት ሲዘጋ እድሉ ሊያመልጠኝ ችሏል ሲል በአገልግሎት መቋረጥ እድሉ እንዳመለጠው”ም ነግሮናል፡፡
በውጭ የግብር ሰናይ ደርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እንደሚሰራ የሚናገረው የደሴ ከተማ ነዋሪው ካሊድ መሀመድ በበኩሉ “ሪፖርቶችን ለመጻፍ እና ከድርጅቶቹ ጋር መልእክት ለመለዋወጥ ኢንተርኔት ወሳኝ ነው፤
በአንዳንድ ባለ ኮከብ ሆቴሎች እና የመንግስት ተቋማት በባለ ገመድ ኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰራባቸው ነበሩ ሆኖም በርካታ ሰው ስለሚጠቀም የኢንተርኔቱ ፍጥነት ዝቅተኛ በመሆኑ አንድ ፋይል ለመላክ ምናልባትም ግማሽ ቀን መቀመጥ ሊኖርብህ ይችላል” ሲል ችግሩን ያስረዳል፡፡
ከሰሞኑ አመታዊ አፈጻጸሙን ይፋ ያደረገው ኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢውን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት በ21.7% ወይም በ16.7 ቢሊዮን ብር በማሳደግ 93.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
21.79 ቢሊዮን የተጣራ ትርፍ ነው አግኝቻለሁ ያለው ተቋሙ በአማራ ክልል ኢንተርኔት በመቋረጡ ምክንያት ስለደረሰበት ኪሳራ ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል፡፡
በክልሉ የተጣለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብቃቱን ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማስጀመር ከሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ገልጾ ነበር።
ሐምሌ 7፣2016 ዓ.ም በበርካታ የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት አግልግሎት ተለቆ፣ ተጠቃሚዎች የሞባይል ዳታ ማግኘት ችለዋል።
ይሁን እንጅ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን በእነዚህ ከተሞች ስለመልቀቁ በይፋ ያለው ነገር የለም።
አክሰስ ናው" የተባለ አለም አቀፍ ተቋም ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ላይ በጣለችው ገደብ ሳቢያ በፈረንጆቹ 2023 ዓመት “1.59 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የኢኮኖሚ" ጥቅም አጥታለች” የሚል ሪፖርት አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
"አክሰስ ናው እና "ኪፕ ኢት ኦን" የተባሉት ተቋማት በቅንጅት በሰሩት ጥናት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ 2008 ጀምሮ በተለያዩ ስፍራዎች 26 ጊዜ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን በማስረጃ ማረጋገጥ ስለመቻላቸው በመግለጽ ሪፖርት አውጥተው ነበር፡፡
በዚህም “ኢትዮጵያ ኢንተርኔት የማግኘት መብትን በመጣስ በዚሁ አመት በአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር እንደሆነች” በሪፖርታቸው ላይ አመላክተዋል፡፡
የኢንተርኔት ግንኙነትን ማቋረጥ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉ ሰዎችን የመረጃ ግንኙነታቸው እንዲገደብ ከማድረጉ ባሻገር የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተደባብሰው እንዲታለፉ የሚያደርግ በመሆኑ መንግስት በአፋጣኝ አገልግሎቱን እንዲያስጀምርም መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡
አል ዐይን ያነጋገራቸው የኢንተርኔት አገልግሎት ዳግም ተጀምሮባቸዋል የተባሉት ከተሞች ነዋሪዎች የኢንተርኔት አገልግሎቱ ፍጥነት ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር አዝጋሚ ቢሆንም ለጊዜው አዳዲስ መረጃዎችን ለመከታተልና የተቋረጡ ግንኙነቶችን ለማስቀጠል እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡