በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያበቃም ክልሉ አሁንም በኮማንድ ፖስት እየተመራ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ
መንግስት የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብቃቱን በይፋ እንዲናገር የሕግ ባለሙያዎች ጠይቀዋል
ነዋሪዎች በክልሉ ውስጥ ጦርነት፣ የእንቅስቃሴ ሰዓት ገደብ፣ ኬላ ፍተሻ እና ሌሎች ክልከላዎች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው ብለዋል
በአማራ ክልል ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያበቃም ክልሉ አሁንም በኮማንድ ፖስት እየተመራ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን “መልሼ አደራጃለሁ” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ሁኔታው ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።
ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ታውጆ የነበረው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት ከተራዘመ በኋላ ከሁለት ሳምንት በፊት ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡
የአዋጁ የቆይታ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ መንግስት በግልጽ ለህዝቡ ማሳወቅ ግዴታ ነበረበት? ወይስ አልነበረበትም? የሚለው ጉዳይ አሁንም አከራካሪ ሆኗል፡፡
ጠበቃ እና የህግ አማካሪ የሆኑት አቤል ዘውዱ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያልተራዘመው መንግስት ከዚህ በፊት የነበረበትን የጸጥታ ችግር በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት አስኬዳለሁ በማለቱ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች የሚገድብ በመሆኑ የአዋጁ ቆይታ ጊዜ ሲያበቃ ይፋ ለህዝብ ማሳወቅ እንደነበረበት ጠበቃ እና የህግ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጥሎበት የነበረው ህዝብ አዋጁ በግልጽ መነሳቱን ወይም የትግበራ ጊዜው ማብቃቱን የማወቅ መብት አለው ያሉት ባለሙያው ይህ ደግሞ የጸጥታ ሀይሎች በዜጎች ላይ በአስቸኳይ አዋጅ ስም እንግልት እና በደል እንዳያደርሱ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የህግ ባለሙያ በበኩላቸው በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጣሉ ምክንያት መደበኛ የህግ እና ፍትህ ስርዓት መስተጓጎላቸውን ተናግረዋል፡፡
“በአማራ ክልል ጥቅማቸው በህግ ስርዓት እንዲከበርላቸው የሚፈልጉ ደንበኞች አሉኝ” ያሉት ይህ የሕግ ባለሙያው ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አብቅቷል ብዬ ወደ ስራ ለመግባት ባስብም ክልሉ አሁንም ወደ መደበኛ የህግ ስርዓት እንዳልተመለሰ ተረድቻለሁም ብለዋል፡፡
መንግስት በይፋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማብቃቱን ለህዝብ ማሳወቅ እንዲሁም መደበኛ የህግ እና ፍትህ ስርዓት ማስፈን ይጠበቅበታል የሚሉት ባለሙያው ይህ ካልሆነ ደግሞ ክልሉ በይፋ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየተዳደረ ከሆነም በግልጽ ህጉን ተከትሎ ማስወሰን የመንግስት ግዴታ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ይህ ባልሆነበት ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ ባበቃበት እና መደበኛ የህግ ስርዓት ማስፈን ባልተቻለበት ሁኔታ ህዝብን ለተባባሰ የህግ ጥሰት እና እንግልት የሚዳርግ መሆኑን የህግ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካበቃበት ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ህይወት በአማራ ክልል ምን እንደሚመስል ነዋሪዎችን አነጋግረናል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሁለት ወረዳዎች የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ተናገሩ
ስሙ ለደህንነቱ ሲባል እንዳይጠቀስ የፈለፈ የባህርዳር ነዋሪ እንዳለው ከሆነ አሁንም በከተማው ዙሪያ አልፎ አልፎ በከባድ መሳሪያ የታገዘ የተኩስ ልውስጥ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ነዋሪው አክለውም “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አልተራዘመም የሚለውን ወሬ ስንሰማ ደስ ብሎን ነበር ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፣ አሁንም ኢንተርኔት እንደተዘጋ ነው፣ መንገዶች ማታ ማታ ላይ ይዘጋሉ፣ እንቅስቃሴያችንም እንደተገደበ ነው” ብለዋል፡፡
“መደበኛ የጸጥታ ሀይል ተሰማርቶ የተለመደውን ህይወታችንን መቀጠል ናፍቆናል፡፡ ድብርት ውስጥ ነን“ የሚለው ይህ አስተያየት ሰጪ ማታ ማታ ቤታችን እየተንኳኳ ሰዎች ይታሰራሉ፣ ይታገታሉ ገንዘብ ካልከፈሉ መፈታት አይችሉም ሲልም ተናግሯል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ በየቦታው ያለው ፍተሻም ሆነ የጸጥታ ሀይሎች እንቅስቃሴ ምንም የተለየ ለውጥ የለም ብሏል፡፡
“ደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ሰዎችን ይፈትሻሉ፣ በከተማዋ ዙሪያ ደግሞ የፋኖ ታጣቂዎች ሰዎችን እየፈተሹ ያሳልፋሉ አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ እንዳለን ነው” ብለዋል እኝህ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ፡፡
“ትራንስፖርት ገደብ አሁንም እንዳለ ከመሆኑ ባለፈ ባጃጆች ከአንድ ፌርማታ በላይ መጓዝ አይችሉም፣ ምሽት ላይ የተገኘ ወጣት ከተፈቀደልህ ሰዓት በላይ ስትንቀሳቀስ ተገኝተሃል በሚል ለእስር እና ድብደባ ይዳረጋል” ያለን ደግሞ ለደህንነቱ ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የወልደያ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡
አሁንም አልፎ አልፉ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እንደቀጠለ ነው ያለን ይህ አስተያየት ሰጪ እንደ ልባችን ተንቀሳቅሰን ስራ መፈለግ እና መስራት ከባድ በመሆኑ በረሃብ እና ኑሮ ውድነት ልንሞት ነው ሲልም የጦርነቱን ጉዳት ገልጿል፡፡
እንደ ነዋሪው አስተያየት አሁን እየተሄደበት ባለው መንገድ የጸጥታው ሁኔታ ቢባባስ እንጂ አይሻሻልም የሚለው ይህ አስተያየት ሰጪ ለሰላም ዝግጁ ነን ስለተባለ ብቻ ሰላም አይመጣም መሬት ላይ ያለው ነገር እንደዛ አይደለም፣ ተፋላሚዎች ከግል ጥቅም፣ አልሸነፍ ባይነት እና ግትርነት መውጣት አለባቸው ሲል ተናግሯል፡፡
ሌላኛው የጎንደር ከተማ ነዋሪ በበኩሉ የከተማዋ እና ዙሪያ አካባቢ ነዋሪዎች ከኑሮ ውድነቱ በተጨማሪ የመንግስት ሃላፊነት በያዙ፣ በአጋቾች እና ሌቦች እየተሰቃዩ መሆኑን ነግሮናል፡፡
ሸቀጦችን ከአዲ አበባ ጎንደር በተሽከርካሪ በማምጣት በሹፍርና ሙያ ይተዳደር እንደነበር የተናገረው ይህ አስተያየት ሰጪ በየቦታው ባሉ የፍተሻ ጣቢያዎች ላይ በሚደርሱ እንግልቶች ምክንያት ስራ ማቆሙን አክሏል፡፡
“በየ ፍተሻ ጣቢያዎቹ የኮማንድ ፖስት፣ የሚኒሻ እና ሌሎችንም ምክንያቶች እየተጠቀሱ ክፍያ እንጠየቃለን፣ ለምን እና ደረሰኝ ስጡን ስንል ደግሞ እንግልቱ ይብሳል” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አብቅቷል ከተባለበት ጊዜ ወዲህ የጎንደር እና አካባቢው የሰላም ሁኔታ የባሰ መበላሸቱንም ተናግሯል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር አረርቲ ከተማ የሆነችው ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ እንዳለችው በአካባቢው ያለው ጦርነት አሁን ላይ መቆሙን ነገር ግን የእንቅስቀሴ ገደብ አሁንም እንደተጣለ መሆኑን ተናግራለች፡፡
በተለይም ሚኒሻ የሚባሉት የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ወጣቶችን ያለ ምንም ምክንያት እየደበደቡ እና እያንገላቱ ነው የምትለው ይህች አስተያየት ሰጪ የእንቅስቀሴ ገደብ የተጣለው ከምሽት 2 ሰዓት በኋላ ቢሆንም ከ12 ሰዓት ጀምሮ ውጪ ላይ ያገኙትን ሰው እንደሚደበድቡ አክላለች፡፡
ነዋሪዎች ስላነሷቸው ጥያቄዎች እና ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የክልል እና ፌደራል መንግስታትን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በማብቃቱ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የታሰሩ ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
በአማራ ክልል፣ አፋር ክልል አዋሽ አርባ እና በአዲስ አበባ ታስረው የነበሩ ሰዎች ከእስር በመለቀቅ ላይ ሲሆኑ የበይነ መረብ ጋዜጠኞቹ በላይ ማናዬ፣ ቴድሮስ ዘርፉ እና ሌሎችም ከእስር መፈታታቸው አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች እና የሚዲያ ባለሙያዎች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።