ኢራን በኢራቅ በሚገኙ 2 የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የሚሳይል ጥቃት ፈጸመች
በኢራቅ የአሜሪካ የጦር አይሮፐላኖች ማረፊያ በሆኑ ጦር ሰፈሮች ላይ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ኢራን ከደርዘን በላይ ባለስቲክ ሚሳይሎችን አስወንጭፋለች፡፡
የጥቃቱ ሁለት ኢላማዎች አል አሳድ እና ኤርቢል የተሰኙ የጦር ሰፈሮች ናቸው፡፡
ኢራን ጥቃቱን በአሜሪካ ለተገደለባት የጦር መሪዋ ጄነራል ቃሲም ሶሌይማኒ በቀል የተፈጸመ ነው ብላለች፡፡
ከጥቃቱ በኋላ ስለጉዳዩ በአሜሪካው የደህንነት መስሪያ ቤት ፔንታጎን ማብራሪያ የተሰቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁሉም ነገር ደህና ነው ያሉ ሲሆን በጥቃቱ ስለደረሰው ጉዳት ማጣራት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የኢራን ቴሌቪዥን በአንጻሩ በጥቃቱ 80 አሜሪካዊያን አሸባሪዎች ተገድለዋል፤ የኤሪካ ሄሊኮፕተሮችና ወታደራዊ ቁሳቁሶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ዘግቧል፡፡ መረጃውን እንዴት እንዳገኘው ግን የቴሌቪዥን ጣቢያው ያለው ነገር የለም፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ እንደሆነና ከብሄራዊ የደህንነት አማካሪ ቡድናቸው ጋር እየተማከሩ እንደሚገኙም ሮይተርስ በዘገባው ጠቁሟል፡፡አሜሪካ ሁኔታውን ገምግማ የሀገሪቱን ዜጎች እና በቀጣናው የሚገኙ አጋሮቿን ለመከላከል ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃ እንደምትወስድ የፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆናታን ሆፍማን ገልጸዋል፡፡
በኢራቅ ከ5000 በላይ አሜሪካውያን ወታደሮች ከሌሎች አጋር ሀገራት ወታደሮች ጋር በመሆን ለኢራቅ ጦር ስልጠናና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
አሜሪካና አጋሮቿ ከመካከለኛው ምስራቅ ጦራቸውን እንዲያስወጡ ደጋግማ የጠየቀችው ኢራን፣ አሁንም ተጨማሪ እልቂት እንዳይከሰት አሜሪካ ከነ አጋሮቿ ከቀጣናው ለቀው እንዲወጡ አሳስባለች፡፡
ምንጭ፡- ሮይተርስ