የኢራኑ ፕሬዝዳንት የሀገሪቷን ዋና ከተማ በሌላ ከተማ የመቀየር ሀሳብ እንዳለቸው ተናገሩ
ፕሬዝዳንቱ ዋና ከተማውን መቀየር የፈለጉት በቴሄራን ባለው ከፍተኛ የአየር ብክለት እና የመሬት ጥበት ምክንያት ነው
ከ1786 ጀምሮ የኢራን መዲና በመሆን እያገለገለች የምትገኝው ቴሄራን የ9.4 ሚሊየን ዜጎች መኖርያ ናት
የኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዚሽኪያን የኢራንን ዋና ከተማ ለማዘዋወር ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዝዳንቱ በከተማዋ የሚገኙ መሰረታዊ ችግሮች ለሀገሪቱ ርዕሰ መዲናነት እንዳትመጠን እያደረጓት ይገኛሉ ብለዋል።
የመሬት ጥበት፣ የውሀ እጥረት እና ከፍተኛ የአየር ብክለት ለመዲናዋ እድገት እንቅፋት ሆነዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ሀገሪቷ የሚመጥናት አዲስ ዋና ከተማ እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ቴሄራን መፍትሄ ልናበጅላቸው በማንችላቸው ችግሮች ተከባለች የተሻለ አማራጭ የሚሆነው የሀገሪቱን የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ማዕከል ወደ ሌላ ከተማ ማዘዋወር ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ዜጎች ከተማዋን እንዲለቁ ከማድረግ ይልቅ መንግስት መቀመጫውን እና ቢሮውን ቢያዘዋወር ዜጎች ሊከተሉት እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።
የኢራንን ዋና ከተማ የመቀየር ሀሳብ ሲቀርብ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም ከ2005-2013 በስልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዝዳንት ማህሙድ አሀመዲንነጃድ ይህንኑ ሀሳብ አቅርበው ፓርላመዋው ጉዳዩን የሚያጠና ልዩ ካውንስል አቋቁሞ ነበር።
አዲሱ ዋና ከተማ የት ሊሆን እንደሚችል በይፋ ያልተነገረ ሲሆን፤ ከሀገሪቷ ደቡባዊ የባህር ዳርቻ ከተሞች መካከል በአንዱ ሊሆን እንደሚችል ፕሬዝዳንቱ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ዋና ከተማው ዋነኛ የንግድ መተላለፍያ ወደ ሆነው “ፐርዢያን ገልፍ” መጠጋት ቢችል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል።
ፕሬዝዳንቱ “ከባህር ዳርቻዎች ወደ ማዕከላዊ ገበያ የምንጓጉዝበትን ዋጋ ስለሚቀንስ ምርቶችን በተሻለ ዋጋ በገበያ ውስጥ ለማቅረብ ያስችለናል፤ ከዚህ ባለፈም የሀገሪቱ ወጪ እና ገቢ ንግድ በሚካሄድበት አቅራብያ መንግስት መገኝቱ የተሻለ የንግድ ስርአት እንዲኖር ያደርጋል” ብለዋል።
የፕሬዝዳንቱን ሀሳብ የተቃወሙት በ1990 የተሄራን ከንቲባ የነበሩት ጎላምሃሲን ካርባሺ ሀሳቡ አደገኛ መንግስትን በርካታ ወጪ የሚያስወጣ እና ሁለት ከፍተኛ ችግር ያለባቸውን ከተሞች የሚፈጥር ነው ሲሉ ተችተዋል።
ከ1786 ጀምሮ የኢራን መዲና በመሆን እያገለገለች ያለችው ቴሄራን በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የምትገኝ ሲሆን ከካስፒያን ባህር በ100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች።
9.4 ሚሊየን ሰዎች የሚኖሩባት ከተማዋ በኢራን እና በምእራብ እስያ ትልቋ ከተማ ስትሆን በመካከለኛው ምስራቅ ደግሞ ከካይሮ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።