ኢራን በኒዩክሌር ፕሮግራሟ ዙሪያ ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር “የሚያግዳት የለም” - ሃሚኒ
የኢራን ጠቅላይ መሪ ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር በራችን ክፍት ብንሆንም የማይታለፉ ቀይ መስመሮች ግን አሉ ብለዋል
ሃሚኒ ከአዲሱ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ካቢኔ ጋር ተወያይተዋል
ኢራን በኒዩክሌር ፕሮግራሟ ዙሪያ ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን የሀገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ተናገሩ።
ሃሚኒ በዛሬው እለት ከአዲሱ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ካቢኔ ጋር ተወያይተዋል።
በዚህ ውይይትም “ጠላት” ካሏት ጋር አሜሪካ ጋር ለመደራደር “ምንም የሚያግድ ነገር የለም” ቢሉም በድርድሩ ዙሪያ የማይታለፉ ናቸው ያሏቸውን ቀይ መስመሮች ለለዘብተኛው ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን መግለጻቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ዘገባው ስለ ቴህራን ቀይ መስመሮች በዝርዝር ባይጠቅስም ሃሚኒ አሜሪካን “መታመን የሌለባት ሀገር” ሲሉ መግለጻቸውን አክሏል።
በኢራን የውጭ ጉዳይ፣ የኒዩክሌር ፕሮግራምና ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያሳልፉት የ85 አመቱ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ፥ የፔዝሽኪያን ካቢኔ “ጠላትን እንዳያምን” አሳስበዋል።
ሃሚኒ የአሜሪካው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸውን ከ2015ቱ የኒዩክሌር ስምምነት ካስወጡ በኋላ ከዋሽንግተን ጋር ለድርድር ዝግጁ ነን የሚል አስተያየት የሰጡት በዛሬው እለት ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ለሰጡት አስተያየት እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
አሜሪካ እና ኢራን በ2015ቱ የኒዩክሌር ስምምነት ዙሪያ የገቡበትን ፍጥጫ እና በጋዛው ጦርነት ምክንያት የተባባሰውን ውጥረት ለማርገብ በኦማን እና ኳታር ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።
ድርድሩ ውጤት አላስገኝ በማለቱም ኢራን ዩራኒየም የኒዩክሌር መሳሪያ ለመስራት በሚያስችል ደረጃ በማበልጸግ ላይ መሆኗ ተደጋግሞ ተጠቅሷል።
የኢብራሂም ራይሲን በሄሊኮፕተር አደጋ መሞት ተከትሎ በተደረገ ምርጫ ያሸነፉት መሱድ ፔዝሽኪያን ቴህራን ከምዕራባውያን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ እንደሚሰሩ ቃል ገብተው ነበር።
በፔዝሽኪያን አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አባስ አራግቺ እና የቀድሞው አቻቸው ሞሀመድ ዛሪፍ በ2015ቱ የኢራን የኒዩክሌር ስምምነት ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው።
ፕሬዝዳንቱም ሆነ በካቢኔው ውስጥ የተካተቱት ለኒዩክሌር ድርድር ቅርበት ያላቸው ሰዎች ግን ያለ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ፈቃድ የባላንጣዎቹን ቅራኔ ማስተካከል ይችላሉ ተብሎ አይጠበቅም።