ኢራን በሞስኮ ለእይታ ያቀረበችው ድሮን - “ሞሃጀር-10”
ለ24 ስአት መብረር የሚችለው “ሞሃጀር -10” 2 ሺህ ኪሎሜትሮችን በመጓዝ ጥቃት ማድረስ ይችላል ተብሏል
ኢራን በሞስኮ የባለስቲክ ሚሳኤሎች እና ድሮኖችን ጨምሮ አዳዲስና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎቿን ለእይታ አቅርባለች
ኢራን በእስራኤል ላይ እፈጽመዋለው ያለችው የበቀል እርምጃ በሚጠበቅበት ወቅት በሞስኮ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎቿን ለእይታ አቅርባለች።
ለእይታ ከበቁት ውስጥ በራሷ አቅም የተገነባው “ሞሃጀር - 10” የተሰኘ ድሮን ይገኝበታል።
“ሞሀጀር -10” የአሜሪካ ባለስልጣናት ኢራን ለሩሲያ ልካዋለች የሚሉት “ሞሃጀር- 6” ተከታይ ነው።
ግዙፉ ድሮን በሚጓዘው ርቀትም ሆነ በሚሸከመው ተተኳሽ ከዚህ ቀደም ቴህራን ከሰራቻቸው ድሮኖች የተሻለ መሆኑን መኸር የተሰኘው የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።
“ሞሀጀር -10” 2 ሺህ ኮሎሜትሮችን መጓዝ ይችላል፤ አርፎ ሃይል መሙላት ሳይጠበቅበት 24 ስአት ሙሉ ይጓዛል የተባለለት ድሮኑ 300 ኪሎግራም የሚመዝን ተተኳሽ መሸከም እንደሚችልም ተጠቅሷል።
ቴህራን “ሞሀጀር - 6” ከተባለው ድሮን አንጻር የመጫን እና የመጓዝ አቅሙ በእጥፍ የጨመረውን “ሞሀጀር -10” በሞስኮ ለእይታ ያቀረበችው የመካከለኛው ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ነው።
እስራኤል በግዛቴ ውስጥ የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ሃላፊ ኢስማኤል ሃኒየህን መግደሏ ሉአላዊነት እና ክብሬን የተዳፈረ ነው ያለችው ቴህራን አጻፋውን እመልሳለሁ ካለች ሁለት ሳምንታ ተቆጥረዋል።
ከወራት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችና ሮኬቶች ወደ እስራኤል በመተኮስ ያገኘችው ውጤት አመርቂ አለመሆኑም በአሁኑ ወቅት ጊዜ ወስዳ እንድታጤን ሳያደርጋት አልቀረም ይላሉ ተንታኞች።
የኢራን መከላከያ ሚኒስቴር ከድሮኖች ባሻገር ዘመናዊ የራዳር እና የአየር መቃወሚያ ስርአቶችንም በሞስኮ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ ማቅረቧ የዝግጅቷ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ከትናንት ጀምሮ ለሶስት ቀናት ክፍት በሆነው አውደርዕይ ላይ የኤሌክትሮኒክ ውጊያ ስርአቶች፣ የአየር እና ባህር ሃይሎች ጸረ ሚሳኤሎች እንዲሁም ባለስቲክ ሚሳኤሎች ለተመልካቾች ክፍት ሆነዋል ነው የተባለው።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባለፈው ሳምንትም የሀገሪቱ ባህር ሃይል በእስራኤል ላይ ለሚወሰደው እርምጃ ዝግጁ መሆኑንና ከእይታ ተሰውሮ ጥቃት መፈጸም የሚችል ክሩዝ ሚሳኤል መታጠቁን መግለጹ ይታወሳል።
የሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ቴህራን የታጠቀቻቸውን አዳዲስ ሚሳኤሎችና ድሮኖች የሚያሳይ ቪዲዮ ለቋል።