ኢራን ለእስራኤል "የወንጀል ተግባር" ምላሽ ትሰጣለች- የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ዛቻ ስታሰማ እስራኤል ደግሞ ኢራንን አርፈሽ ተቀመጭ እያለች ነው
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በተመድ ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር የእስራኤል ረጅም እጅ ኢራን ውስጥ የማይደርስበት ቦታ የለም ሲሉ አስጠንቅቀዋታል
ኢራን የእስራኤልን የወንጀል ተግባር ዝም ብላ እንደማታልፈው የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናሰር ከናኒ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ይህን ያሉት እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሄዝቦላን መሪ ሀሰን ነስረላህ እና የኢራንን ጋርድ ምክትል አዛዥ መግደሏን ተከትሎ ነው።
እስራኤል ባለፈው አርብ እለት በቤሩት በፈጸመችው የአየር ጥቃት ከሄዝቦላ መሪ ሰኢድ ሀሰን በተጨማሪ ብርጋጄር ጀኔራል አባስ ኒልፎሮሽያንም ተገድለዋል።
እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ በሄዝቦላ ታጣቂዎች ላይ እና የመን ውስጥ በሀውቲ ላይ እየፈጸመች ያለው ጥቃት መባባስ ከቁጥጥር ወጭ ወጥቶ ኢራንን እና የእስራኤል ዋነኛ አጋር የሆነችውን አሜሪካን ወደ ጦርነቱ ጎትቶ ያስገባል የሚል ስጋት እንዲያይል አድርጎታል።
"ጠላትን ሊያጸጽት የሚችል ጠንካራ እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ ካናኒ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ተናግረዋል። ካናኒ አክለው እንዳላሉት ኢራን ጦርነት አትፈልግም፤ ነገርገን አትፈራም።
ኢራን ሁኔታውን ከሊቢኖሰ አመራሮች ጋር እየተነጋገረች እና በቅርበት እየተከታተለችው ነው ብለዋል ካናኒ።
ባለፈው ጥቅምት ወር የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ድንበር ጥሶ በእስራኤል ላይ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት እስራኤል በጋዛ ከፍተኛ ውድመት አድርሳለች። እስራኤል በጋዛ ዘመቻዋ በርካታ የሀማስ መሪዎችን ገድላለች።
የቡድኑ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ኢራን ውስጥ ተገድሏል። ኢራን እና ሀማስ ለሀኒየህ ግድያ እስራኤልን ተጠያቂ ቢያደርጉም እስራኤል ግን ግድያውን ስለመፈጸሟ ወይም ስላለመፈጸሟ በይፋ ያለችው ነገር የለም።
እስራኤል አሁን ላይ ትኩረቷን ወደ ሊባኖስ በማዞር የሄዝቦላ ይዞቻዎች ናቸው በምትላቸው ቦታዎች መጠነሰፊ የአየር ጥቃት ከፍታለች።
ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ዛቻ ስታሰማ እስራኤል ደግሞ ኢራንን አርፈሽ ተቀመጭ እያለች ነው።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በተመድ ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር የእስራኤል ረጅም እጅ ኢራን ውስጥ የማይደርስበት ቦታ የለም ሲሉ አስጠንቅቀዋታል።