በእስራኤል- ሄዝቦላህ ግጭት፤ አዳሩን ምን አዳዲስ ክስተቶች ተስተናግደዋል?
በሊባኖስ የአየር ድብዳበዎች የቀጠሉ ሲሆን፤ በ24 ሰዓት ብቻ ከ100 በላይ ሰዎች ተገድለዋል
በማእከላዊ ቤሩት በተፈጸመ የአየር ድብደባ 3 የፍሊስጤም ህዝባዊ ነጻ አውጪ ግንባር አመራሮች ተደግለዋል
በእስራኤል እና በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው የሄዝቦላህ ቡድን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እያገረገሸ እና መጠነ ሰፊ ጉዳት ማስከተሉን እንደቀጠለ ነው።
በሊባኖስ የመገናኛ መሳርያዎች ላይ የተገጠሙ ፈንጂዎችን በማፈንዳት ጥቃት ማድረስ የጀመረችው እስራኤል ካሳለፍነው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ መጠኑ ከፍ ያለ የአየር እና የሚሳኤል ጥቃት በሊባኖስ ላይ እየፈጸመች ትገኛለች።
ሄዝቦላህ ለእስራኤል እየሰጠ በሚገኝው ምላሽ እስከዛሬ በቡድኑ ጥቅም ላይ ውለው የማያውቁ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ጭምር በመጠቀም በማዕከላዊ እስራኤል ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል።
ዳሩን ምን አዳዲስ ክስተቶች ተስተናግደዋል?
እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ የሄዝቦላህ ኢላማዎች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃቶች የቀጠለች ሲሆን፤ ትናንት እሁድ ምሽት ብቻ 120 የሄዝቦላህ ኢላማዎችን ማጥቃቷን አስታውቃለች።
እስራኤል በምእራባዊ የቤሩት ከተማ ከምታደርገው የአየር ድብደባ በተጨማሪ በትናትናው እለተ ማእከላዊ ቤሩት የሚገኘውን ኮላ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ድብደባ ፈጽማለች።
የፍሊስጤም ህዝባዊ ነጻ አውጪ ግንባር (PFLP) ባወጣው መግለጫ እስራኤል በቤሩት ከተማ ኮላ አካባቢ በፈጸመችው የአየር ድብደባ ሶስት አመራሮቹ መገደላቸውን አስታውቋል።
በእስራኤል የአር ድብደባ የተገደሉ የፍሊስጤም ህዝባዊ ነጻ አውጪ ግንባር አባላትም
-መሃመድ አብደል-አል (አቡ ጋዚ)፤ የፒ.ኤፍ.ኤል.ፒ የፖለቲካ ቢሮ አባልና የወታደራዊ ደህንነት ክፍል ኃላፊ
- ኦማድ ኦዴህ (አቡ ዚያድ)፤ የፒ.ኤፍ.ኤል.ፒ ወታደራዊ ክፍል አባልና በሊባኖስ የቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ
- አብዱል ራህማን አብዴል አላል- የፒ.ኤፍ.ኤል.ፒ አባል ናቸው።
በትናንት እሁድ በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከ105 በላይ ሰዎች በእስራኤል የአየር ድብደባ መገደላቸውን ያስታወቀው የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር፤ 359 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ብሏል።
ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ ከ14 በላይ የህክምና ባለሙያዎች መገደላቸውን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፤ እስካን በእስራኤል የአየር ድብደባ የሞቱ ሊባኖሳውያን ቁጥር ከ1 ሺህ መሻገሩንም ገልጿል።
የእስራኤል- ሄዝቦላህ ግጭት ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ
የእስራኤል ጥቃት በመላው ሊባኖስ ከፍተኛ ስጋትን እና ውጥረትን የፈጠረ ሲሆን፤ በደቡብ እና ምስራቅ ሊባኖስ ውስጥ የሚኖሩ በርካቶችም መኖሪያቸውን ለቀው እየወጡ ይገኛሉ።
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ፤ እስከ አንድ ሚሊየን የሚደርሱ ሊባኖሳውያን ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል።
የተባሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ፤ በሊባኖስ ውስጥ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን መፈናቀላቸውን አስታውቀው፤ ከ50 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገር ሶሪያ መሰደዳቸውን አስታውቀዋል።
ከ70 ሺህ በላይ እስራኤላውያንም በሄዝቦላህ እና እስራኤል ድንበር ላይ የተኩስ ለውውጥ ከተጀመረ ወዲህ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል።