ኪም ጆንግ ኡን በህክምና ላይ ናቸው ወይስ አርፈዋል?
ኪም ጆንግ ኡን በህክምና ላይ ናቸው ወይስ አርፈዋል?
ከሰሞኑ የሰሜን ኮሪያው ዋና ሰው ኪም ጆንግ ኡን ህክምና ላይ መሆናቸውን የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡ ኪም የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ሲደረግላቸው ስለመቆየታቸውም መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ቀዶ ህክምና ሲደረግላቸው ቆይቶ አረፉ የሚሉ ዜናዎች የወጡት፡፡
ዋሺንግተን ፖስት ከዋሺንግተንና ሲኡል ባለሥልጣናት ስለ ሰሜን ኮሪያው መሪ ሞት አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ ኪም መሞታቸው ተረጋግጧል ሲሉ ሌሎች መገናኛ ብዙሃንም ዝግበዋል፡፡ እነዚሁ መገናኛ ብዙሃን፣ በጉዳዩ ላይ ከፒዮንግ ያንግ የተሰማ ነገር አለመኖሩ ጉዳዩን ወደ እውነት አስጠግቶታል እያሉ ናቸው፡፡
የሰሜን ኮሪያ ማዕከላዊ ብሮድካስቲንግ ጣቢያ ኪም ጆንግ ኡን የሶሻሊስት ኃይልን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት አስተዋፅኦ አድርገዋል ለተባሉ ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል የሚል ዘገባ ቢያሰራጭም የተጠቀማቸው ፎቶግራፎች ግን ቀድሞ ከነበራቸው የተገኘ እንጂ በዕለቱ የተነሱት አይደለም ተብሏል።
ኪም እንደ አውሮፓውያኑ ባሳለፍነው ሚያዝያ 11 የገዥውን ፓርቲ የሰራተኞች ቡድን ስብሰባ ከመሩ በኋላ ለሁለት ሳምንት ያህል በአደባባይ አልታዩም፡፡ የሰሜን ኮሪያ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ኪም ያሉበትን ቦታ አልያም የጤና ሁኔታቸውን አልጠቀሱም፤ አላሳወቁም፡፡
ኪም ለሳምንታት በተከበረውና ፀሃያማው ቀን በሚባለው በአባታቸው ልደት ስም የሚከበረው ዝግጅት ላይ አለመገኘታቸው የመሞታቸው ዜና እውነት ሊሆን ይችላልም እያስባለ ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ የሰሜን ኮሪያ ፈላጭ ቆራጭ፣ የዓለም ልዕለ ሀያላት የውዝግብ ስበት ማዕከል የሆኑት ኪም ከ2012 ጀምሮ የሰራተኞች ፓርቲ ሊቀመንበርም ናቸው።
የ36 ዓመቱ የሰሜን ኮርያ መሪ ከባድ የልብ ቀዶ ጥገና ማድረጋቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ህይወታቸው እንዳለፈ እየዘገቡ ያሉ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን ተበራክተዋል። ይህ የሞት ዜና እውነት የሚሆን ከሆን እህታቸው ኪም ዮ ጆንግ ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚረከቡም ነው እየተዘገበ ያለው፡፡ እህታቸው ኪም ዮ ጆንግ እንደ ወንድማቸው ኪም ጆንግ ኡን ሁሉ ሚሳዬል የማስወንጨፍ የተለየ ፍላጎት አላቸው ይባላል።
የኪም ጆንግ ኡንን መሞትም ሆነ አለመሞት በተመለከተ የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙሃን ያሉት ነገር የለም፡፡ በተመሳሳይ የፒዮንግያንግን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት ሲኤን ኤን፣ ቢቢሲና አልጀዚራ በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር የለም፡፡ የዋሸንግተን ፖሰቶቹ ሳይመን ድንየር፣ ጆን ሁድሰንና ሚን ጆ ኪም ግን ከደቡብ ኮሪያና አሜሪካ ሹሞች መሞታቸውን ሰምተናል ብለው ጽፈዋል፡፡
ምንጭ፡- ዋሺንግተን ፖስት