አሜሪካ፣ እስራኤል የያዘችው እቅድ እንዲራዘም የፈለገችው፣ ተጨማሪ ኃይሏ መካከለኛው ምስራቅ እስከሚደርስ ነው ተብሏል
እስራኤል በጋዛ ለማድረግ ያቀደችውን የእግረኛ ጦር ዘመቻ በአሜሪካ ጥያቄ መሰረት ማራዘሟን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
አሜሪካ፣ እስራኤል በጋዛ ላይ በእግረኛ ጦር ጥቃት ለመክፈት የያዘችው እቅድ እንዲራዘም የፈለገችው፣ ተጨማሪ ኃይሏ መካከለኛው ምስራቅ እስከሚደርስ ነው።
ነገርግን አሜሪካ ሌላም ምክንያት እንዳላት የሚጠቁም ዘገባም ወጥቷል።
የፕሬዝደንት ባይደን አስተዳደር እስራኤል የማይቀረውን ጋዛን በእግረኛ ጦር የማጥቃት እቅድ እንድታራዝም የፈለገው ተጨማሪ በሀማስ የታገቱ እንዲለቀቁ እና የስብአዊ እርዳታ ጋዛ እንዲደርስ በመፈለግ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል።
በሀማስ ተይዘው የነበሩ ሁለት አሜሪካውያን ሰዎች መለቀቅ ተይዘው ያሉት 200 ገደማ ሰዎች ይለቀቃሉ የሚል ተስፋ ሰጥቷል።
በእስራኤል- ሀማስ ጦርነት ከእስራኤል ጎን የሆነችው አሜሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ አቅሟን ለማሳየት እና እስራኤልን ለመደገፍ ሁለት ግዙፍ የጦር መርከቦቿን ወደ ሜድትራኒያን ባህር ማስጠጋቷ ይታወሳል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ በ50 አመታ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ እስራኤል እየወሰደች ያለው የአጸፋ ጥቃት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
እስራኤል በሀማስ ይዞታ በሆነችው ጋዛ፣ በሰሜን እስራኤል በኩል ከሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ እና በዌስት ባንክ ባሉ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት እየሰነዘረች ነው።
እስራኤል በአሁኑ ወቅት ጋዛን በመክበብ በእግረኛ ወታደር ለማጥቃት እና የሀማስ ታጣቂዎችን ለመግደል ተዘጋጅታለች።
የአረብ ሀገራት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ቢያቀርቡም እስካሁን ሰሚ አላገኙም።