
ስለ ቀጣይ ጊዜ ኢንቨስምት፣ ቴክኖሎጂ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በኢነርጂና በንግድ አጋርነት ላይ መክረዋል
የአረብ ኢምሬትስ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪና የአቡዳቢ ምክትል አስተዳዳሪ ሼክ ታኖን ቢን ዛይድ አል ናህያን ከአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የአረብ ኤምሬትስ እና አሜሪካ በፋይናንስ እና በላቁ ቴክኖሎጂዎች ፣አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ፣ኢነርጂ እና መሠረተ ልማት ዘርፎች ያለው ትብብር የሁለቱንም ሀገራት ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
በውይይቱ ላይም ሼክ ታኖን ቢን ዛይድ አል ናህያን አረብ ኤምሬትስ እና አሜሪካ በተለያዩ መስኮች ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው፤ በሁለቱም ሀገራት መካል በተለይም በፋይናንስ እና በንግድ ዘርፎች ከፍተኛ ትብብር እንዳለ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአረብ ኢምሬትስ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪና የአቡዳቢ ምክትል አስተዳዳሪ ሼክ ታኖን ቢን ዛይድ አል ናህያን በአሜሪካ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ጉብኝቱ ከ54 ዓመታት በፊት በጀመረው የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑም ተነግሯል።
በጉብኝቱ ወቅት ሼክ ታህኖን ቢን ዛይድ አል ናህያን ከዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይፋዊ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ተይዟል።
በዚሁ ወቅትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊና ቴክኖሎጂያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይደረጋል።
በተጨማሪም በአሜሪካ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል ላለፉት አስርት ዓመታት የዘለቀውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ በሚቻልበት መንገዶች ላይ እንደሚወያዩም ይጠበቃል።
ጉብኝቱ በሀገራቱ መካከል እያደገ ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት የሚያጠናክር እንዲሁም እርስ በርስ በመደጋገፍ እና በሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት መካከል በሚደረጉ ውይይቶች ለማጠናከር የሚያግዝ ነው ተብሏል።