
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሼክ ታህኖን ቢን ዛይድን በዋይት ኃውስ ተቀብለው አነጋረዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትምፕ “ከአረብ ኢምሬትስ ጋር ያለን ግንኙነታችን በታሪክ ጠንካራ ነው” አሉ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙትን የአረብ ኢምሬትስ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪና የአቡዳቢ ምክትል አስተዳዳሪ ሼክ ታህኖን ቢን ዛይድ አል ናህያንን በዋይት ኃውስ ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዋይት ኃውስ በነበራቸው ቆይታም በሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት፣ በፀጥታ፣ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ትብብርን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ሼክ ታህኖን ቢን ዛይድ በአረብ ኤምሬትስ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በማውሳት፤ በመካከለኛው ምስራቅ እና በአለም ላይ ደህንነትን እና መረጋጋትን ለማስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከውይይቱ በኋ በትሩዝ በማህበራዊ ገጻቸው ላይ “ዛሬ ምሽት በዋይት ሀውስ ሼክ ታህኖን ቢን ዛይድ አል ናህያንን በዋይት ኃውስ ተቀብያለሁ፤ በርካታ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ስብሰባዎች እና የእራት ግብዣ አድርጌያለሁ” ብለዋል።
ትራምፕ አክለውም "በምሽቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት እና ጠንካራ ወዳጅነት ያሳየ ነበር" ብለዋል።
"የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ እና በአለም ላይ ሰላም እና ደህንነትን ለማስፈን በጋራ የሚሰሩ የሁልጊዜ አጋር ናቸው" ሲሉም ገልጸዋል።
የአረብ ኢምሬትስ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪና የአቡዳቢ ምክትል አስተዳዳሪ ሼክ ታኖን ቢን ዛይድ አል ናህያን በአሜሪካ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ጉብኝቱ ከ54 ዓመታት በፊት በጀመረው የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑም ተነግሯል።
በጉብኝቱ ወቅት ሼክ ታህኖን ቢን ዛይድ አል ናህያን ከዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይፋዊ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ የተያዘ ሲሆን፤ በትናናው እለትም ከአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በዚሁ ወቅትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊና ቴክኖሎጂያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገዋል።