በመካከለኛው ምስራቅ ዋና ዋና “ጥላት” ያለቻቸውን ቡድኖች ያዳከመችው እስራኤል ቀጣይ ትኩረት ኢራን ወይስ ሌላ?
በቀጠናው የበሽር አላሳድ መንግስት መውደቅን ጨምሮ የሀማስ እና ሄዝቦላህ መዳከም የእስራኤልን ቀጠናዊ የበላይነት አጠናክሯል
ዘገባዎች በ2025 የኔታንያሁ አስተዳዳር የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም መግታት ላይ ሊያተኩር እንደሚችል እየገለጹ ነው
ጥቅምት ሰባቱ የሀማስ ጥቃት በመካከለኛው ምስራቅ በርካታ የሀይል አሰላለፍ ለውጦችን ያስከተለ ሁነት የተስተናገደበት ነው፡፡
ለተፈጸመባት ጥቃት በጋዛ ከአመት ለሚበልጥ ጊዜ ጦርነት የከፈተችው እስራኤል በፍልስጤም ሳትወሰን በሊባኖስ ሶሪያ እና የመን ወታደራዊ ዘመቻዎችን አድርጋለች፡፡
ዋነኛ “ጥላት” የምትላት ኢራን የአካባቢው አጋሮች በዚህ ጦርነት በከፍተኛ ደረጃ ከመዳከማቸው ባለፈ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዎ መሪዎቻቸውን በሞት ተነጥቀዋል፡፡
በተጨማሪም እስራኤል ከሀማስ ጋር ጦርነቱን በድርድር ካጠናቀቀች በኋላ በጋዛ ሰርጥ ወታደራዊ ቁጥጥሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል ይጠበቃል፡፡
እነዚህ ሁነቶች ለኔታንያሁ አስተዳደር ቀጠናዊ የበላይነትን ሲያላብሱ የበሽር አላሳድ መንግስት ውድቀትን ጨምሮ ሀማስ እና ሄዝቦላህ የተዳከሙባት ኢራን ተጽዕኖንን ቀንሷል፡፡
2025 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤት መመለስ እና ተያያዥ ጉዳዮች ይህን የእስራኤል የበላይነት የሚያጎለብት እንደሚሆን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህን ተከትሎም ኔታንያሁ የኢራንን የኒዩክሌር ምኞቶች እና የሚሳኤል መርሃ ግብሮች እውን እንዳይሆኑ እንዲሁም በእስራኤል ስትራቴጂካዊ ስጋቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እንደሚያስችላቸው ተነግሯል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ተንታኞች ወቅታዊ ሁኔታዎች ቴሄራን በኒውክሌር ፕርግራም መቀጠል እና ከምዕራባውያን ጋር መደራደር በሚሉ አጣብቂኞች ውስጥ ከተዋታል እያሉ ነው፡፡
የአለም አቀፍ ክራይስስ ግሩብ የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ጆስት ሂልተርማን ኢራን ለእስራኤል ጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ይናገራሉ፡፡
ዳይሬክተሩ ቴሄራን በኒዩክሌር ፕሮግራሞቿ ላይ ማሻሻያዎችን ገቢራዊ ካላደረገች ኔታንያሁ እና ትራምፕ በኒዩክሌር ማብላያ ጣብያዎች ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ የሚችሉበት እድል ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በ 2024 ማብቂያ ላይ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ለ14 ወራት የዘለቀው የጋዛ ጦርነት እና በግዛቱ ውስጥ የተያዙ የእስራኤል ታጋቾችን ነፃ ለማድረግ ከሃማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነትን እንደሚፈራረሙ ለድርድሩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ጠቁመዋል ።
ቀጥሎም የእስራኤል ጦር ሰርጡን ጥሎ መውጣት ሀማስ ዳግም እንዲደራጅ እና እንዲታጠቅ ያደርጋል በሚል ጦሯን በአካባቢው እንዲቆይ ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ኔታንያ ከአዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ጋር በመሆን በኢራን ላይ ሙሉ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው እንደሚሆን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡