እስራኤል በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ የፈጸመችው ጥቃት ያደረሰው ጉዳት ዝቅተኛ መሆኑን ቴሄራን ገለጸች
ንጋታ ላይ እስራኤል በኢራን የሚሳይል ማምረቻ ፋብሪካዎች እና ሌሎች ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች
ኢራን የአየር መከላከያዎቿ የእስራኤልን ጥቃት በተሳካ ሁኔታ ማክሸፍ እንደቻሉ እና የደረሰውም ጉዳት የተወሰነ ነው ብላለች
እስራኤል በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ የፈጸመችው ጥቃት ያደረሰው ጉዳት ዝቅተኛ መሆኑን ቴሄራን ገለጸች።
እስራኤል በዚህ ወር መጀመርያ አካባቢ ከኢራን ለተፈጸመባት የሚሳኤል ጥቃት የአጸፋ እርምጃ ነው ያለችውን ጥቃት ዛሬ ማለዳ ላይ በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ፈጽማለች፡፡
"የኢራን አገዛዝ በእስራኤል ላይ ለወራት በተከታታይ ላደረሳቸው ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት በአሁኑ ጊዜ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በኢራን ውስጥ በሚገኙ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ የተጠኑ ጥቃቶችን እየፈፀመ ነው” ሲል የእስራኤል ጦር ጥቃቱን አስታውቋል።
ከሰዓታት በኋላ የእስራኤል ጦር ጥቃቱ መጠናቀቁን እና አላማውን ማሳካት መቻሉን ተናግሯል። የኢራን መገናኛ ብዙሀን እስራኤል በቴህራን ላይ ለወሰደችው እርምጃ “ተመጣጣኝ ምላሽ” እንደሚሰጥ ባለስልጣናት መናገራቸውን ዘግበዋል፡፡
የአየር መከላከያ ስርዓቷ ከእስራኤል የተሰነዘረውን ጥቃት በተሳካ ሁኔታ መከላከል ችሏል ያለችው ኢራን በበኩሏ በቴህራን፣ ኩዜስታን እና ኢላም ግዛቶች በሚገኙ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ይፋ አድርጋለች፡፡
ሀማስ በጥቅምት 7 በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በታሪካዊ ባላንጣዎቹ ቴሄራን እና ቴልአቪቭ መካከል ያለው ውጥረት ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡
እስራኤል ከባለፈው ወር ጀምሮ በሊባኖስ በአየር እና በዕግረኛ ጦር የምታደርሰው ጥቃት ተጠናክሮ በቀጠለበት የአካባቢው ውጥረት እየተባባሰ መምጣት ኢራን እና አሜሪካን በቀጠናው ግጭት ተሳታፊ እንዳያደርግ ከፍተኛ ስጋት አንዣቧል፡፡
የእስራል ጦር በማለዳው ጥቃት ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን ጥቅም ላይ ስለማዋሉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኢላማዎች የኢነርጂ መሠረተ ልማቶችን እና የኢራንን የኑክሌር ጣብያዎችን አለማካተታቸው የተነገረ ሲሆን “ኢራን ከዚህ ቀደም የሰራችውን ስህተት በመድገም በእስራኤል ላይ ጥቃት የምትፈጸም ከሆነ ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንገደዳለን” ብሏል ጦሩ፡፡
ሀይማኖታዊ መሪው አያቶላ አሊ ሀሚኒ ሰራዊቱ ለማንኛውም የእስራኤል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በርካታ እቅዶችን እንዲያዘጋጅ ትዕዛዝ ስለመስጠታቸው ትላንት መዘገቡ ይታወሳል።
የኢራን ባለስልጣናት እስራኤል በኢራን የኑክሌር እና የነዳጅ ማውጫ ስፍራዎች ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ኢራን የአጸፋ ምላሽ ትሰጣለቸ ብለው ነበር።
ነገር ግን የእስራኤል ጥቃት በወታደራዊ ካምፖች፣ የሚሳይል መጋዘኖች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ብቻ ላይ የተገደበ ከሆነ ኢራን ምላሽ እንደማትሰጥ ተናግረው ነበር።
ከዚህ ባላፈም በወታደራዊ ካምፖች እና መጋዘኖች ላይ የተገደበው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰም ኢራን የበቀል እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ተነግሯል፡፡