መካከለኛው ምስራቅ እስራኤል ኢራን ለፈጸመችባት ጥቃት የምትሰጠውን ምላሽ በመጠበቅ ጭንቅ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል
እስራኤል ሲጠበቅ የነበረውን ጥቃት በኢራን ላይ መፈጸሟ ተዘገበ።
እስራኤል ኢራን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለፈጸመችባት የባለስቲክ ሚሳይል ጥቃት ለመበቀል ዛሬ ማለዳ ጥቃት መፈጸሟን ሮይተርስ ዘግቧል።
ጥቃቱ በእስራኤል እና ኢራን መካከል ያለውን ውጥረት የበለጠ ያከረዋል ተብሏል።
የኢራን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በዋና ከተማዋ ቴህራን እና በአቅራቢያዋ በሚገኙ ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች ላይ ለበርካታ ሰአታት የቆየ ፍንዳታ መከሰቱን ዘግበዋል። ነገርግን እስካሁን በጥቃቱ የተጎዳ ሰው ስለመኖሩ እና ስለደረሰው ውድመት አልዘገቡም።
የእስራኤል መንግስት ቴሌቪዥን ቀደም ብሎ ሶስት ዙር የአየር ጥቃቶች መጠናቀቃቸውን እና ዘመቻው ማብቃቱን መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል። መካከለኛው ምስራቅ እስራኤል ኢራን በ200 ገደማ ሚሳይሎች ለፈጸመችባት ጥቃት የምትሰጠውን ምላሽ በመጠበቅ ጭንቅ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።
የመካከለኛው ምስራቅ ተቀናቃኝ በሆኑት እስራኤል እና ኢራን መካከል ውጥረት የተጀመረው፣ የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ነው።
ሀማስ ሊባኖስ ውስጥ በሚንቀሳቀሰው እና በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላም ይደገፋል።
አሁን ላይ የእስራኤል አጋር የሆነችው አሜሪካ እና ኢራን ወደ ቀጣናዊ ግጭቱ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።