እስራኤል ለምትፈጽመው የአጸፋ ጥቃት ኢራን ምን አይነት ዝግጅት እያደረገች ነው?
ኢራን በኑክሌር ጣብያዎቿ እና ከፍተኛ የጦር መሳርያ ክምችት በሚገኝባቸው ወታደራዊ ካምፖች ላይ የአየር መቃወሚያዎቿን እያጠናከረች ነው
እስራል በኢራን ላይ በምትወስደው የበቀል እርምጃ ቁጥራቸው እስከ አንድ ሺህ የሚጠጉ ባላስቲክ ሚሳይሎችን ልታስወነጭፍ እንደምትችል ተገምቷል
ኢራን ከእስራኤል ለሚሰነዘርባት የበቀል ጥቃት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች እንደምትገኝ ተነገረ፡፡
የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስረላህ ግድያን ተከትሎ የቡድኑ ዋነኛ አጋር የሆነችው ቴሄራን በእስራኤል ቁጥራቸው 180 የሚደርስ የባላስቲክ ሚሳኤሎችን መተኮሷ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ስተዝት የሰነበተችው እስራኤል የምትፈጸምው የጥቃት መጠን እና ኢላማዎቿ ቀጣዩን የቀጠናውን ሁኔታ ይወስናል በሚል የአካባቢውን ውጥረት አንሮታል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ ከኢራን ባለስልጣናት አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ሀገሪቱ ከቴልአቪቭ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመመከት እና ከእዚያ በኋላ ስለሚኖሩ ምላሾች ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ሀይማኖታዊ መሪው አያቶላ አሊ ሀሚኒ ሰራዊቱ ለማንኛውም የእስራኤል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በርካታ እቅዶችን እንዲያዘጋጅ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
ባለስልጣናቱ ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንዳረጋገጡት እስራኤል በኢራን የኒውክሌር እና የነዳጅ ማውጫ ስፍራዎች ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ኢራን የአጸፋ ምላሽ የምትሰጥ ሲሆን፤ ነገር ግን የእስራኤል ጥቃት በወታደራዊ ካምፖች፣ የሚሳኤል መጋዘኖች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ብቻ የተገደበ ከሆነ ኢራን ምላሽ እንደማትሰጥ አብራርተዋል።
ከዚህ ባላፈም በወታደራዊ ካምፖች እና መጋዘኖች ላይ የተገደበው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰም ኢራን የበቀል እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ተነግሯል፡፡
ቴሄራን እና ቴልአቪቭ የሚገኙበት ውዝግብ ወደ ቀጠናዊ ግጭት እንዳያድግ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ስታደርግ የሰነበተችው አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ማብላያ ጣብያዎች እና በነዳጅ ማውጫዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጸም ከእስራኤል ማረጋገጫ አግኝታለች፡፡
ኢራን የአሜሪካ የጦር ካምፖች የሚገኙባቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለእስራኤል ሚሳይሎች እና የጦር አውሮፕላኖች የአየር ክልላቸውን እንዳይፈቅዱ የሰጠችው ማስጠንቀቂያም ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡
ያም ሆኖ ከእስራኤል ለሚሰነዘር ከፍተኛ የአጸፋ ምላሽ የምታደርገውን ዝግጅት አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
ሰራዊቱ 24 ሰአት በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ ትዕዛዝ የተሰጠው ሲሆን ከፍተኛ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች በሚገኙባቸው እና በኒውክሌር ጣብያዎቿ ላይ የአየር መቃወሚያ ስርአቶቿንም በማጠናከር ላይ ትገኛለች፡፡
እስራኤል በኢራን ላይ በምትወስደው የበቀል እርምጃ ቁጥራቸው እስከ አንድ ሺህ የሚጠጉ ባላስቲክ ሚሳይሎችን ጥቅም ላይ ልታውል እንደምትችል ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል