“በሱዳን ወረራ ጉዳይ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝምታን መምረጡ አሳዛኝ ነው”- አቶ ደመቀ መኮንን
የኢትዮ-ሱዳን “የድንበር ውዝግብ” በድርድር ሊፈታ እንደሚገባም ልዩ መልእከተኛው ተናግረዋል
የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልእክተኛው ሀቬስቶ “የኤርትራ ሰራዊት መውጣትን ሂደት መፍጠን” አለበት ብለዋል
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ህብረት ልዩ መልእክተኛውና የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሀቪስቶ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች መክረዋል፡፡
የትግራይ ጉዳይን በቀዳሚ አጀንዳነት አንስተው የተወያዩት ሚኒስትሮቹ በክልሉ በመደረግ ላይ ስላሉ ሰብዓዊ እርዳታዎች እና የህግ ተጠያቂነት ሁኔታዎች ላይ ነው የመከሩት፡፡
በክልሉ በመደረግ ላይ ካሉት ሰብዓዊ እርዳታዎች 70 በመቶ ያህሉን የኢትዮጵያ መንግስት መሸፈኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እስካሁን ለ4.5 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ ለማቅረብ ተችሏል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ሁለተኛ ዙር እርዳታዎችን ለማድረግ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ወደ ስራ መገባቱንም ገልጸዋል።
ሆኖም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ያህል ድጋፍ እያደረገ እንደዳይደለ አልሸሸጉም፡፡
በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር መንግስት ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር ለመስራት ዝግጁ ከመሆኑ በሻገር ከአሁን ቀደም በማይካድራ እና በአክሱም የተፈጸሙ ጥሰቶችን በመረመረው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንበኩል እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ይህ መንግስት አሉ የተባሉ ጥሰቶች በገለልተኛ አካላት እንዲመረመሩ እና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክት ነው አቶ ደመቀ የተናገሩት፡፡
የአውሮፓ ህረት ልዩ መልዕክተኛው ፔካ ሃቪስቶ በበኩላቸው አሁንም ቢሆን ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በህብረቱ በኩል ያለውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና ተመድ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ያደነቁም ሲሆን በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ይህንንም ከእርዳታ ድርጅቶች ለመረዳት መቻላቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
የሚዲያ አካላት በክልሉ ተገኝተው እንዲዘግቡ መደረጉንም በአዎንታነት ጠቅሰዋል፡፡
ሆኖም አሁንም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች እርዳታዎች እንዲደርሷቸው ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት ሃቪስቶ፡፡
የኤርትራ ሰራዊት መውጣት ጉዳይ እንዲፋጠንም ጠይቀዋል። ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል።
አቶ ደመቀ በበኩላቸው በመንግስት በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ከመጪው የዝናብ ወቅት በፊት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም እንዲቻል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።
የኤርትራ ወታደሮች እንደሚወጡ የማድረጉ ሂደት እንዲፋጠን እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።
በወጣው የምህረት ቀነ ገደብ “እጅ ያልሰጡ ወንጀለኞችን ወደ ህግ ለማቅረብ እየሰራን ነው”ም ነው አቶ ደመቀ ያሉት፡፡
ሚኒስትሮቹ በግድብ የድርድር ሂደት ላይም ተወያይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድርድሩ በውጤት እንዲጠናቀቅ ላደረጉት ጥረት ለወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ከበሬታ ያላት መሆኑን አቶ ደመቀ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይም በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ቁርጠኛ መሆኗን ጭምርም ነው አቶ ደመቀ የገለጹት።
ድርድሩ በአውሮፓ ህብረት፣ በአሜሪካ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ታዛቢነት እንደሚካሄድም አብራርተዋል፡፡
የውሃ ክፍፍል ጉዳይ በሶስቱ አገራት መካከል ብቻ የሚካሄድ ካለመሆኑም በላይ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነው የሚል አቋም በኢትዮጵያ በኩል እንዳለ ያብራሩም ሲሆን ድርድሩ በግድቡ የውሃ ሙሌት ላይ ማተኮር እንዳለበት ግልጽ አድርገዋል፡፡
ሀቬስቶ በበኩላቸው ድርድሩ በመጪው ክረምት ከሚከናወነው የውሃ ሙሌት በፊት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን ተስፋ በመግለፅ በህብረት በኩል የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል “የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ”ን ሁለቱ አገራት በድርድር መፍታት እንደሚገባቸው ነው ልዩ መልእክተኛው ያነሱት።
አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው “ሱዳን የኢትዮጵያን ልዑላዊ መሬት በወረራ መያዟን ተከትሎ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን በይፋ አለማውገዙ የሚያሳዝን” ነው ያሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ችግሩ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ ጽኑ አቋም ያለ መሆኑን አስርድተዋል ከጽህፈት ቤታቸው እንደተገኘው መረጃ።
የአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል ልዩ መልዕከተኛ የሆኑት ሃቪስቶ ከሁለት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡