ለ2ኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ከፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ጋር ተወያዩ
የፊንላንዱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሀቪስቶ የአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል ልዩ መልዕከተኛ መሆናቸው ይታወቃል
ልዩ መልዕክተኛው ፔካ ሀቪስቶ እና ልዑካቸው ወደ ትግራይ የማቅናት ዕቅድ እንዳለው ተነግሯል
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጆሴፕ ቦሬል ልዩ መልዕክተኛ እና የፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶ ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያ ገቡ፡፡
ዛሬ ከግብጽ ወደ አዲስ አበባ የገባው እና በሃቪስቶ የሚመራው የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጋር በብሔራዊ ቤተ መንግስት መምከሩን የፕሬዝዳንቷ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ሀቪስቶ እና ልዑካቸው ወደ ትግራይ ክልል ተጉዘው አሁናዊ የክልሉን ሁኔታ ለማየት ማቀዳቸውን ጽ/ቤቱ አስታውቋል።
ሀቪስቶ በክልሉ ባለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነት እና የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ እንዲሁም በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የመወያየት ዕቅድ አላቸውም ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ በምክክራቸው ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ለመንግስታትም ሆነ ለዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ለመገናኛ ብዙኃን የትግራይን ሁኔታ እንዲመለከቱ ጥሪ ማድረጉን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ክልል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን እርዳታ በራሱ አቅም እያዳረሰ መሆኑን ስለመግለጻቸውም ጽ/ቤቱ በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።
በሕግ ማስከበር ዘመቻው “ተከሰቱ” የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም ለማጣራት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው ፕሬዘዳንት ሣህለ ወርቅ የተናገሩት።
ሃቪስቶ ከአሁን ቀደምም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበረ፡፡ በዚያን በጎረቤት ሃገር ሱዳን ጭምር ጉብኝት አድርገው ከባለስልጣናቱ ጋር ጭምር ተወያይተው ነበረ፡፡
አሁንም በድጋሚ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም ከድንበር ጋር በተያያዘ ከሱዳን ጋር ያለውን ችግር በተመለከተ ሁኔታዎችን እንዲያጤኑ በህብረቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል መላካቸው ነው የተነገረው፡፡
ሃቪስቶ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት በግብጽ ካይሮ ቆይታ አድርገዋል፡፡ ከአረብ ሊግ ዋና ጸሃፊ አቡል ጌይት ጋር ጥሩ ቆታ ማድረጋቸውንም ነው በትዊተር ገጻቸው ያስታወቁት፡፡
ልዩ መልዕክተኛ በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ “አሳሳቢ” መሆኑን ገልጸዋል፡፡