"ኢትዮጵያ...በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን የሚያቅብ ማናቸውም ዓይነት ስምምነት አትፈርምም" ውጭ ጉዳይ
የሁለቱ ሀገሮች አካሄድ የአፍሪካ ህብረትን ሚና የሚያሳንስ መሆኑን እና የኪንሻሳው ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁን ኢትዮጵያ ገልጻለች
ሚኒስቴሩ "ግብጽ እና ሱዳን አለን የሚሉትን የውሃ ክፍፍል የሚያጸና አስገዳጅ ስምምነት ካልተደረሰ የሚል ግትር አቋም ይዘዋል" ብሏል
በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ እየተከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ስለሚቀጥልበት ሁኔታ ለመመካከር በኪንሻሳ የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
ስብሰባውን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስትመጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ፣ ስብሰባው ያለፉትን ሂደቶች በመገምገም ድርድሩ የሚቀጥልበትን ሂደት ለመወሰን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጿል። ም/ጠ/ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በስብሰባው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የድርድር ሂደት እንዲቀጥል እና በውጤት እንዲጠናቀቅ የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግ አሳውቀዋል ብሏል መግለጫው። ናይል የድንበር ተሻጋሪ ኃብት እንደመሆኑ የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሃዊና ምክንያታዊ መርህ መሰረት ባደረገ አኳኋን የመጠቀም መብት እንዳላቸውም አስምረውበታል። በዚህም መሰረት በተፋሰሱ ላይ የሰፈነው የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ብቸኛ ተጠቃሚነትን የማስቀጠል ፍላጎት መቀየር ያለበት በመሆኑ ሂደቱን በትብብር እና መግባባት መወሰን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዳሴ ግድብ የትብብር ዕድል የፈጠረ ሀገራዊ ፕሮጄክት በመሆኑ በድርድር ሂደቱ የተደረሱ የአቋም መቀራረቦችን ከዳር ማድረስ እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡
በስብሰባው ሶስቱም ታዛቢዎች (ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት) በታዛቢነት እንዲቀጥሉ ስምምነት የተደረሰ ሲሆን፣ ስለሚኖራቸው ሚና ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። በዚህ ረገድ ሶስቱ ሀገራት የየራሳቸውን አቋም ያንጸባረቁ ሲሆን ፣ እንደ መግለጫው ከሆነ ኢትዮጵያ ሀገራቱ ሙሉ ባለቤት የሆኑበትን እና የአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍን የሚያስጠብቅ የድርድር ሂደት በመደገፍ ታዛቢዎች በሶስቱ ሀገራት በጋራ ስምምነት ሲጠየቁ ብቻ ሃሳብ ማቅረብ ለመፍቀድ ተስማምታለች፡፡ ግብጽ እና ሱዳን ታዛቢዎች ከአፍሪካ ህብረት እኩል ተሳትፎ የማድረግ ሚና ሊሰጣቸው ይገባል በሚል ያቀረቡት ሀሳብ ተቀባይነት እንዳላገኘ ተገልጿል፡፡ የሁለቱ ሀገሮች አካሄድ የአፍሪካ ህብረትን ሚና የሚያሳንስ መሆኑን ነው መግለጫው ያመለከተው።
በስብሰባው ማጠናቀቂያ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ ምክርቤት ሊቀመንበር ፣ የቀረበውን ረቂቅ መግለጫ (communique) ኢትዮጵያ በመሰረቱ ለመቀበል መስማማቷን ገጻለች፡፡ በአንፃሩ፣ ግብጽ እና ሱዳን በሁለቱ ቀናት ውይይት ያልተነሱ ጉዳዮችን ካልተካተቱ በሚል ረቂቁን አለመቀበላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም፣ ሁለቱ ሀገራት የአፍሪካ ህብረት ሂደትን የሚያሳንስ እና ጉዳዩን ከህብረቱ የሚያወጣ ስልት በመከተል እንዲሁም ምክክር የተደረገባቸውን ጉዳዮች የያዘ መግለጫ አንቀበልም በማለት ድርድሩ አዎንታዊ ውጤት እንዳይኖረው እንቅፋት ሆነዋልም ይላል ።
የውጭ ጉዳይ ያወጣው መግለጫ እንደሚለው "የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዓመት ሙሌት በመርሆዎች መግለጫ መሰረት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይከናወናል፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በግድቡ የሁለተኛ ዓመት ሙሌት ዙሪያ ተገቢውን መረጃ ለመቀያየር ዝግጁቷን በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡ ሁለቱ ሀገሮች ስምምነት ሳይደረስ ግድቡ መሞላት የለበትም በሚል የሚቀርብ አቋም የሕግ መሰረት የሌለው እንዲሁም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ የግድቡ አሞላል እና ተያያዥኛ የውሃ እለቃቅ ስርዓት ላይ ለመስማማት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ዝግጁ ብትሆንም ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር እና ውጤቱ የኢትዮጵያን የውሃ ድርሻ የሚገድብ እና አለን የሚሉትን የውሃ ክፍፍል የሚያጸና አስገዳጅ ስምምነት ካልተደረሰ የሚል ግትር አቋም ይዘዋል። ኢትዮጵያ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የሆነ የአሁን እና የወደፊት በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን የሚያቅብ ማናቸውም ዓይነት ስምምነት አትፈርምም።"
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝደንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሰብሳቢ ፕሬዝደንት ፌሊክስ ሼሲኬዲ እና ቡድናቸው ድርድሩን ለማስቀጠል ያሳዩትን ብርቱ ጥረት የኢትዮጵያ መንግስት በከፍተኛ አክብሮት እንደሚመለከተው በመግለጫው ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ የድርድሩ ሒደት የሀገራቱን ሙሉ ባለቤትነት በሚያረጋግጥ እና የአፍሪካ ህብረትን የማስተባበር ሚና በተሟላ አኳኋን የሚያስጠብቅ የሶስትዮሽ ድርድር ለመከተል ዝግጁ መሆኗንም አስታቃለች። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር በሚያቀርቡት ጥሪ በቅርቡ ስብሰባው እንደሚቀጥል ትጠብቃለች በመግለጫው እንደተጠቀሰው።