በመንግስት ጥሪ በቦሌ ሃገር ቤት የገባ አካል ይህን መጠየቁ ግራ የሚያጋባ ነው-የፓርቲው ሊቀመንበር
ኦፌኮ ጃዋር መሀመድ የዜግነቱን ሁኔታ የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያቀርብ ጠየቀ
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) ጃዋር መሀመድ ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዳለው የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያቀርብ ስለመጠየቁ አስታውቋል። ጥያቄው ምርጫ ቦርድ ከሰሞኑ በጻፈው ደብዳቤ መሰረት የቀረበ ነው ያሉት የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ምላሽ እንዲሰጥበት በሚል የደብዳቤው ኮፒ ለጃዋር መላኩን ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል፡፡
ሆኖም ቦርዱ የጃዋርን ዜግነት መጠየቁ ሊቀመንበሩን ያሳመነ አይመስልም፡፡
መንግስት ግቡና አግዙን ባለው መሰረት ’በባሌ ሳይሆን በቦሌ’ ወደ ሃገር ቤት የገባን፣ በፓርቲ አመራርነት ያልተቀመጠንና በምርጫ ገና ያልተወዳደረን አካል እንዲህ ማለቱ ግራ የሚያጋባ ነው ያሉም ሲሆን ስሙም፣መልኩም ኦሮሞ/ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጃዋር ከሃገር ከወጣ ዘለግ ያሉ አመታትን ማስቆጠሩንና አሜሪካዊ ዜጋ መሆኑን፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማድረግ ሲል ዜግነቱን እንደሚመልስ ከአሁን ቀደም ማስታወቁን በመጥቀስ አል ዐይን አማርኛ ስለቦርዱ ጥያቄ ተገቢነት ላቀረበላቸው ጥያቄም የኢትዮጵያ መንግስት አባረረው እንጂ ወዶ ከሃገር አልወጣም ሲሉ መልሰዋል፡፡