ቤዞስ ወንድሙን በማስከተል በ11 ደቂቃው የጠፈር ጉዞ እንደሚሳተፍ አስታውቋል
የግዙፉ የበይነ መረብ የግብይት ተቋም አማዞን መስራች እና ባለቤት ጄፍ ቤዞስ ወደ ጠፈር ሊጓዝ ነው ተባለ፡፡
“ወደ ጠፈር መጓዝን ከልጅነቴ ጀምሮ ሳልመው ነበር” ያለው ቁጥር አንዱ የዓለማችን ቢሊዬነር በቀጣዩ ወር ወንድሙን ማርክ ቤዞስን አስከትሎ ወደ ጠፈር እንደሚጓዝ አስታውቋል፡፡
ጄፍ ‘ብሉ ኦርጂን’ የተሰኘ የሮኬት ኩባንያ ባለቤት ነው፡፡ ኩባንያው በቀጣዩ ወር 11 ደቂቃዎችን የሚፈጅ የመጀመሪያውን የጠፈር ጉዞ ያደርጋል፡፡
ጉዞው 6 ሰዎችን የሚይዙ 6 መቀመጫዎች ባሏትና ‘ኒው ሼፓርድ’ በተሰኘችው መንኮራኩር የሚደረግ ነው፡፡
‘ኒው ሼፓርድ’ ከ60 ዓመታት በፊት ወደ ጠፈር የተጓዘውን የመጀመሪያውን አሜሪካዊ ጠፈርተኛ (አስትሮኖት) አለን ሼፓርድን ለማስታወስ ለመንኮራኩሯ የተሰጠ የመታሰቢያ ስም ነው፡፡
የወርሃ ሃምሌ መባቻው የጠፈር ጉዞም አለን ሼፓርድ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጠፈር የተጓዘበትን ቀን ታሳቢ ያደርጋል፡፡
የጉዞ ወንበሮቹን ለመሸጥ የሚያስችልና የፊታችን አርብ የሚጠናቀቅ ጨረታ በኩባንያው በኩል በይፋ ዛሬ ተከፍቷል፡፡
በጨረታው ከ143 ሃገራት የተውጣጡ 6 ሺ ገደማ ሰዎች ያመለከቱ ሲሆን የአንድ መቀመጫ (ጉዞ) ዋጋ ወደ 3 ሚሊዮን ዶላር ገደማ መድረሱን ኩባንያው አስታውቋል ፡፡
የዚህ ጉዞ አካል ሆኖም ነው ጄፍ ወደ ጠፈር የሚያቀናው፡፡
የ200 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት የሆነው ቤዞስ ከአማዞን ኃላፊነቱ ለቆ ወደተለያዩ ጠፈር ተኮር ስራዎች እንደሚያተኩር በቅርቡ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ ጠፈር የሚደረጉ የጉብኝት የቱሪዝም ጉዞዎች ተበራክተዋል፡፡ የብዙሃኑን ቀልብ በመግዛት ላይ ያሉት እነዚህ ጉዞዎች የዓለማችንን ተጠቃሽ ቱጃሮች ቀልብ እየገዙም ነው፡፡
ለዚህም ቁጥር ሁለቱን የዓለማችንን ቱጃር፤ የስፔስ- ኤክስ መስራችና ባለቤት እንዲሁም የቴስላ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኩባንያ ዋና አስፈጻሚውን ኤለን መስክን ጨምሮ የቨርጂን ግሩፕ ባለቤቱን እንግሊዛዊውን ሪቻርድ ብራንሰንን መጥቀስ ይቻላል፡፡