የአማዞን ቀጣይ ስራ አስፈጻሚ ይሆናል የተባለው ኤንዲ ጄሲ ማነው?
የዓለማችን ቁጥር ሁለቱ ቱጃር ጄፍ ቤዞስ በመጪው ክረምት ዋና ስራ አስፈጻሚነቱን ለሌላ እንደሚያስረክብ ማስታወቁ ይታወሳል
የአማዞንን የድረገጽ ግብይት አገልግሎቶች ከማስተዋወቅ አልፈው ለስኬት ካበቁ ቁልፍ የተቋሙ አመራሮች መካከል አንዱ ነው
ዛሬ መነጋገሪያ ከሆኑ የቴክኖሎጂ እና የቢዝነስ ዜናዎች መካከል አንዱ የግዙፉ የዓለማችን የበይነ መረብ ግብይት ተቋም አማዞን መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ ኃላፊነቱን ለሌላ እንደሚያስረክብ ማስታወቁ ነው፡፡
ከዓለማችን ቁንጮ ቱጃሮች መካከል 2ኛው የሆነው ቤዞስ በመጪው ክረምት ኃላፊነቱን ለአማዞን የ ‘ክላውድ ኮምፒውቲንግ’ ስራ ክፍል ኃላፊ ኤንዲ ጄሲ እንደሚያስረክብ ዛሬ አስታውቋል፡፡
ከተጠቀሰው ቀን በኋላ በስራ አስፈጻሚዎች ሊቀመንበርነት እንደሚቀጥልም ነው የ57 ዓመቱ ቢሊዬነር ያስታወቀው፡፡
ቤዞስ በሌሎች ተጓዳኝ የቢዝነስ ስራዎች በተለይ በጠፈር የመንኮራኩር ጉዞ አገልግሎቶች ላይ የማተኮር ውጥን አለውም ተብሏል፡፡
ቤዞስ ከኤለን መስክ በመቀጠል በ188 ቢሊዬን ዶላር የዓለማችን ቁጥር ሁለት ቱጃር ነው፡፡
ለመሆኑ ይህ የ1 ነጥብ 7 ትሪሊዬን ዋጋ ያለው ግዙፍ የበይነ መረብ ቸርቻሪ ተቋምን ለመገንባት የቻለው የረብጣ ገንዘብ ባለቤት ይተካኛል ያለው የ53 ዓመቱ ኤንዲ ጄሲ ማነው?
ኤንዲ ጄሲ ክላውድ ኮምፒውቲንጉ አለቃ
የኒውዮርክ ተወላጁ እና የሃርቫርድ ተመራቂው የቢዝነስ ሰው ጄሲ ያኔ አማዞን እየታወቀ መምጣት በጀመረበት እ.ኤ.አ በ1997 ነበር በጀማሪ ሰራተኛሪነት ድርጅቱን የተቀላቀለው፡፡
ግብይትን ጨምሮ በተለያዩ የአመራርነት እርከኖች ያገለገለ ሲሆን በፈረንጆቹ ሚሊኒዬም መባቻ ግድም በነበሩት ዓመታት ከሌሎች 57 ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የአማዞንን የድረገጽ ግብይት አገልግሎት አስጀምሯል፡፡
የአገልግሎቱ ምክትል ሃላፊ ከዚያም ዋና ኃላፊ በመሆንም ሰርቷል፡፡
ድርጅቱ የመረጃ ቋትን መሰረት ባደረጉ አገልግሎቶች(‘ክላውድ ኮምፒውቲንግ’) ልቆ እንዲወጣ ካስቻሉ የድርጅቱ አመራሮች መካከል አንዱ መሆኑ ይነገራል፡፡
አማዞን ባለፈው ዓመት ከ‘ክላውድ ኮምፒውቲንግ’ አገልግሎቱ 45.37 ቢሊዬን ዶላር ገቢ አስገብቷል፡፡ ገቢው ቀደም ካሉት ዓመታት ብልጫ ያለው ነው፡፡ 386 ቢሊዬን ዶላር ይተጋል ከተባለለት የድርጅቱ አመታዊ ገቢም የ12 በመቶ ድርሻ አለው፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ መምጣት አማዞንን ለመሳሰሉ የግብይት ተቋማት ከፍተኛ የገበያ አጋጣሚን ይዞ መጥቷል፡፡
1.3 ሚሊዬን ተቀጣሪዎች ያሉት ይህ ድርጅት ትናንት ይፋ ባደረገው የተጠናቀቀው ዓመት የገቢ አፈጻጸም ሪፖርት 7.2 ቢሊዬን ዶላር ዓመታዊ የተጣራ ገቢ እንዳገኘ አስታውቋል፡፡
ቤዞስ በእሱ እምነት አለኝ ሲል የምስክነት ቃል የሰጠለት ኤንዲም ይህን ከፍተኛ ገቢ የሚያስገባ ተቋም የመምራት ትልቅ ኃላፊነት ነው የተጣለበት፡፡
ከቤዞስ ጋር ቅርበት ኖሮት ጥቂት ለማይባሉ ዓመታት መስራቱ ምናልባትም የተሻለ ሆኖ ተቋሙን ለመምራት ያስችለው ይሆናል በሚል ተነግሯል ተገምቷልም፡፡