“በኢትዮጵያ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የሚፈጥሩት የስራ እድል እያደገ ነው”- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
የበይነ መረብ ግንኙነት ችግር ለመፍታት የቴሌኮምን ዘርፉን በከፊል ወደ ግል የማዞር ስራ እየተሰራ ነውም ተብሏል
የኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ አካል የሆነው የዲጂታል ቴክኖሎጂ የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ
በኢትዮጵያ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች (ስታርትአፕስ) የሚፈጥሩት የስራ እድል እያደገ መምጣቱ ተገለፀ።
የዱባይ የንግድ ምክር ቤትና ኢንዱስትሪ፣ ከዱባይና ሰሜን ኤሚሬትስ የኢትዮጵያ ቆንስል ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ አካል የሆነው የዲጂታል ቴክኖሎጂ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱ በዲጂታል ኢትዮጵያ፣ በጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች፣ በወጣት የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
የዱባይና ሰሜን ኢሚሬትስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል አምባሳደር እየሩሳሌም አምደማርያም ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችላትን መደላድል እየፈጠረች መሆኑን ተናግረዋል።
ግብርና፣ የማምረቻ ዘርፍ፣ ቱሪዝምና የአገልግሎት ዘርፍ ላይ ቅድሚያ የሰጠው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎ እየተፈጠሩ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ 2025 ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ) በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችና የዘርፉ ስራ ፈጠራ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የዘርፉ ማነቆዎችን የሚፈቱ የትራንዛክሽን አዋጅ መፅደቅ፣ የኢኖቬሽን ፈንድ አዋጅ ወደ መጠናቀቅ መቃረቡና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ስራ ፈጠራ በፍጥነት እያደገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የዱባይ ንግድ ምክር ቤትና ኢንደስትሪ የአለም አቀፍ ቢሮ ዳይሬክተር ኦማር ካህን ኢትዮጵያ ለስራ ፈጣሪዎችና ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ወሳኝ ሰዓት ላይ ትገኛለች ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዲጂታል አማካሪ ሜሪያም ሰይድ የበይነ መረብ ግንኙነት ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ የቴሌኮምን ዘርፉን በከፊል ወደ ግል የማዞር ስራ በሂደት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
የበይነ መረብ ግንኙነት መሰረተ ልማት፣ የዲጂታል እውቀትና የዲጂታል ኢኮኖሚ አስቻይ ሁኔታዎች ላይ በመድረኩ ወይይት ተደርጓል።
በመድረኩ ከ19 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ 300 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዙሪያ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ምክክር ተደርጎበታል።