ኬንያዊቷ የዓለም ሪከርድ ባለቤት አግነስ ቲሮፕ ሞታ ተገኘች
ቲሮፕ በስለት ተወግታ ሳትሞት እንዳልቀረ ሲ.ኤን.ኤን አንዳንድ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል
በቅርቡ በተካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ከእነ ጉዳፍ ጸጋዬ ጋር ብርቱ ፉክክርን አድርጋ የነበረችው ቲሮፕ በመኖሪያ ቤቷ ነው ሞታ የተገኘችው
ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት አትሌት አግነስ ቲሮፕ ዛሬ ጠዋት በመኖሪያ ቤቷ ሞታ ተገኘች፡፡
የ25 ዓመቷ ቲሮፕ ምናልባትም ራሷን አጥፍታ ሊሆን እንደሚችል አትሌቲክስ ኬንያ አስታውቋል፡፡
የ10 ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት በሆነችው በአትሌቷ ህልፈተ ህይወት እጅግ ማዘኑንም ነው ያስታወቀው፡፡
“ኬንያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ነጥረው በመውጣት ላይ ከነበሩ እንቁ ወጣት አትሌቶቿ መካከል አንዷን ዛሬ አጣች” ሲልም ነው አትሌቲክስ ኬንያ ሃዘኑን የገለጸው፡፡
ቲሮፕ በስለት ተወግታ ሳትሞት እንዳልቀረ ሲ.ኤን.ኤን አንዳንድ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
በ2015ቱ የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና ደምቀው ከታዩ አትሌቶች መካከል አንዷ የነበረችው ቲሮፕ በቅርቡ በተካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ኬንያን ወክለው ከነበሩ አትሌቶች መካከል አንዷ ነች፡፡
ሲፋን ሃሰን ባሸነፈችው እና ሄለን ኦቢሪ ሁለተኛ ጉዳፍ ጸጋዬ ደግሞ ሶስተኛ ሆነው ባጠናቀቁት የ10 ሺ ሜትር ርቀት ላይ ብርቱ ፉክክርን በማድረግ በአራተኛነትም ነው ያጠናቀቀችው፡፡
ባሳለፍነው ወርሃ መስከረም በጀርመን በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አዲስ ክብረ ወሰንን ለማስመዝገብም ችላ ነበረ፡፡