የቶኪዮ ኦሎምፒክ የሜዳሊያ ሰንጠረዥን እየመሩ ያሉ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
በዘንድሮው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ለሚያሸንፉ ስፖርተኞች 5 ሺህ ሜዳሊያዎች ለሽልማት ተዘጋጅተዋል
ኢትዮጵያ በ1 የወርቅ ሜዳሊያ ከዓለም 40ኛ፤ ከአፍሪካ 3ኛ ደረጃ ለይ ተቀምጣለች
በጃፓን አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 32ኛው የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ ከተጀመረ ዛሬ 8ኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
የቶክዮ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች መጀመሩን ተከትሎም በርካታ ውድድሮች ፍጻሜ አያገኙ ሲሆን፤ በርካታ ሀገራም የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ጀምረዋል።
በዚህም መሰረት ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ቻይና የሜዳሊያ ሰንጠረዡን በ21 የወርቅ፣ 13 የብር እና 12 የነሃስ በድምሩ በ46 ሜዳሊያዎች በመምራት ላይ ትገኛለች።
ጃፓን ደግሞ በ17 የወርቅ እና በ5 የብር እና 8 የነሃስ በድምሩ በ30 ሜዳሊያዎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ አሜሪካ በ16 የወርቅ፣ 17 የብር እና 13 የነሃስ በድምሩ በ46 ሜዳሊያዎች 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ሩሲያ በ11 የወርቅ፣ 15 የብር እና 11 የነሃስ ሜዳሊያዎች 4ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፤ አውስትራሊያ ደግሞ በ10 የወርቅ፣ 3 የብር እና 14 የነሃስ ሜዳሊያዎች 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ብሪተኒያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድስ እና ኒውዚላንድ ደግሞ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከ6ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ ያለውን ይዘዋል።
በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ በ1 የወርቅ እና 2 የብር ሜዳሊያዎች ከዓለም 25ኛ ስትሆን ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ ላይ ተቀምጣለች፤ ቱኒዚያ በ1 የወርቅ እና በ1 የብር ከዓለም 30ኛ ከአፍሪካ 2ኛ፤ ኢትዮጵየ ደግሞ በ1 የወርቅ ሜዳሊያ ከዓለም 40ኛ ከአፈሪካ ደግሞ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች።
እስካሁን ባለው መረጃም 74 ሀገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት መቻላቸውን ከስፍራው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በዘንድሮው የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ከ205 ሀገራት የተውጣቱ ከ11 ሺህ በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ከስፍራው ተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ 33 አይነት ስፖርታው ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን፤ በውድድሩ ለሚያሸንፉ አትሌቶችም 5 ሺህ ሜዳሊያዎች ለሽልማት ተዘጋጅተዋል።