ንጹህ ሃይል” ለአለማችን ሰፊ የገበያ እድል ይፈጥራል - ጆን ኬሪ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የአየር ንብረት ጉዳዮች አማካሪው ጆን ኬሪ ፥ የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ሆነው ለተሾሙት ሱልጣን አል ጀበር ድጋፋቸውን ሰጥተዋል
አትላንቲክ ካውንስል ያዘጋጀው አለም አቀፍ የኢነርጂ ፎረም በአቡ ዳቢ እየተካሄደ ነው
አለማችን ካሏት የገበያ እድሎች ሁሉ ትልቁን የንጹህ ሃይል ገበያ ልትጠቀምበት እንደሚገባ የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ አሳሰቡ።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የአየር ንብረት ጉዳዮች አማካሪው ጆን ኬሪ ፥ አትላንቲክ ካውንስል ባዘጋጀው አለም አቀፍ የኢነርጂ ፎረም ላይ ንግግር አድርገዋል።
አለማችን በበካይ ጋዝ ልቀት ፈተና ውስጥ ወድቃለች ያሉት ጆን ኬሪ፥ ባለፉት ሁለት አመታት የተከናወኑ የአየር ንብረት ጉባኤዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንደታዩባቸው አንስተዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ መንገዶች የሚመድብ በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ሃብት እንዳይባክንም ሀገራት በትኩረት እንዲሰሩ ነው ያሳሰቡት።
“በዘርፉ የሚፈስ መዋዕለ ንዋይ ቀላል አይደለም፤ ፋይዳውም ትልቅ መሆኑን መረዳት አለብን፤ አለማችን የንጹህ ሃይል ገበያን ልትጠቀምበት ግድ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
አቡ ዳቢ በየአመቱ የአትላንቲክ ካውንስል አለም አቀድ የኢነርጂ ፎረምን ታስተናግዳለች።
ሁለተኛ ቀኑን በያዘው ጉባኤ በኢነርጂ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዘርፎች የካበተ ልምድ ያላቸው የበርካታ ሀገራት ውሳኔ ሰጪ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
ጆን ኬሪ በዚሁ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ሆነው ለተሾሙት ሱልጣን አል ጀበርም ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
“አል ጀበር ብርቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተቆርቋሪ ነው” ያሉት ኬሪ፥ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በንጹሃ ሃይል ልማት ላይ ላስመዘገበችው ውጤትም የአል ጀበር አስተዋጽኦ ግዙፍ መሆኑንም አብራርተዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በ2015 በፓሪስ የተደረሰውን የአየር ንብረት ለውጥ መግቻ ስምምነት በመፈረም ቀዳሚዋ ናት።
ለዚህም 15 ቢሊየን ዶላር በመመደብ በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ በስፋት እየሰራች እንደምትገኝ ተገልጿል።