የአብን የፓርላማ አባላት በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ነው ያሉት "መንግስታዊ እገታና ስወራ" በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቁ
በመሆኑም ጉዳዮቹ በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል
አባላቱ እየተደረገ ያለው በአማራ ሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ጠያቂዎችን የማጥፋትና አንገት ማስደፋት ነው ብለዋል
በአማራ ክልል "በሕግ ማስከበር ስም እየተደረገ ነው" ያሉት "አፈናና ወከባ" እንዲቆም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠየቁ፡፡
አባላቱ እየተደረገ ያለው ሕግ ማስከበር ሳይሆን "በአማራ ሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ጠያቂዎችን የማጥፋትና ሕዝባችንን አንገት ማስደፋት ነው" ሲሉ እርምጃውን በመቃወም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በመግለጫው መንግስት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ህዝባችን ማንነትን መሰረት ላደረጉ ጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ መፈናቀልና ስደት፣ ለንብረት ውድመትና ለዘርፈ ብዙ ሥነልቦናዊ ችግሮች ተጋልጦ ይገኛል ብለዋል፡፡
አባላቱ ሕዝባችን "በትሕነግና ምስለኔዎቹ" ኅልውናው አደጋ ላይ በወደቀበት በአሁኑ ጊዜ "በነቁ አማሮች" ማለትም በአብን አባላትና አመራሮች፣ በፋኖ አባላትና አገራቸውንና ሕዝባቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ባገለገሉ የጦር መኮንኖች ላይ "ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የአፈና፣ የሕገ-ወጥ እስር እና የመንግስታዊ እገታ ሥራዎች ላይ መጠመዱ አሳዝኖናል"ም ብለዋል በመግለጫው፡፡
ይህ "ከፖለቲካዊ ሴራ በጸዳ አኳኋን" የሚደረግ እንዳልሆነ በመጠቆምም እየተደረገ ያለው ሕግ ማስከበር ሳይሆን በአማራ ሕዝብ የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችንና ጠያቂዎችን የማጥፋትና ሕዝባችንን አንገት የማስደፋት እንቅስቃሴ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ጉዳዩን በቸልታ እንደማይመለከቱትና እንደሚታገሉትም ነው በመግለጫው ያነሱት፡፡
በመሆኑም በመፈጸም ላይ ነው ያሉት "መንግስታዊ እገታና ስወራ" በአስቸኳይ እንዲቆምና የታገቱ አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ካልሆነ አገርና ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀው የአገራዊ ምክክር ከወዲሁ እንዲጨናገፍ የሚያደርግ ውጤት እንደሚያስከትል አሳስበዋል።
ሕግ ማስከበርን ሰበብ በማድረግ የፌደራል የፀጥታ መዋቅር "ክልሉን በሕገ-ወጥ መንገድ ለመቆጣጠር" የሚያደርገውን ያቁም ያሉም ሲሆን የክልሉ መንግስት ተባባሪ ከመሆን ወጥቶ ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"በሕግ ማስከበር ሰበብ ከተሞችን የጦር አውድማ የማድረግና ንጹሐንን መግደል መንግስታዊ ሽብር በመሆኑ መንግስት የሚያደርገውን ይሄን ሕገወጥ የሽብር ሥራ በአስቸኳይ አቁሞ ሕዝባችንን በማወያዬት የሕዝብ ፍላጎቶችና ድምጾች እንዲሰሙ እንጠይቃለን"ም ነው አባላቱ ያሉት፡፡
አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ለአማራ ሕዝብ ያላቸውን አጋርነት እንዲያሳዩና የአማራ ሕዝብ ውስጣዊ አንድነቱን እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“መንግስት ግድያ ከሚፈጽሙ ኃይሎች ራሱን መነጠሉን ማረጋገጥ አለበት”-አብን
ህገ ወጥ ተግባራት ተበራክተዋል ያለው የአማራ ክልል መንግስት ከሰሞኑ ህግ የማስከበር እርምጃዎችን መጀመሩን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ሆኖም እርምጃው የአማራን ህዝብም ሆነ ሃገሪቱን ከህወሓት ወረራ ለመታደግ ጉልህ አስተዋጽዖ አበርክተዋል በሚል የሚነገርላቸውን በየደረጃው ያሉ የፋኖ አደረጃጀቶች ትጥቅ ለማስፈታትና ለማዋከብ ይባስ ብሎም ለማጥፋት ነው መባሉ ብዙ ግርታን ፈጥሯል፡፡
በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ ያሉ የፋኖና የአብን አባላትና አመራሮች እየታገቱ ነው መባሉም ሲያነጋግር ነበረ፡፡
ከእርምጃው ጋር ስለመያያዙ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም የቀድሞው የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ማሞ ባሳለፍነው ሰኞ ታፍነው ወደ ባህር ዳር መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ለአል ዐይን መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡
ሆኖም "የአማራ ክልል መንግሥት የጦር መሳሪያ አያስፈታም" ሲሉ ከሰሞኑ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)"ሕግ ስናስከብር ፋኖን ለማዋከብ አይደለም፤ እንዲህ የሚባለው ውሸት ነው፤ እኛ ሕገወጦችን እንጂ ፋኖዎችን የመንካት ዓላማ የለንም" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የአብን የፓርላማ አባላት እርምጃውን በተመለከተ ስላወጡት መግለጫ የክልሉን ምላሽ አግኝቶ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
የአብን የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለን እና የቀድሞ ፕሬዝዳንቱን ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)ን ጨምሮ አምስት አባላቱ 6ኛውን ሃገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ፓርላማ መግባታቸው ይታወሳል፡፡