መንግስት የታገቱ ተማሪዎችን የማስለቀቅ ጥረት ባለመጀመሩ ገንዘብ ወደ ማሰባሰብ ገብተናል-የታጋች ቤተሰቦች
ከስምንት ቀን በፊት በኦሮሚያ ክልል ገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ከ100 በላይ ተማሪዎች እና መንገደኞች በታጣቂዎች መታገታቸው ይታወሳል
እገታውን የፈጸሙት አካላት ልጆቻቸው እንዲለቀቅላቸው ከ500 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ተናግረዋል
መንግስት የታገቱ ተማሪዎችን የማስለቀቅ ጥረት ባለመጀመሩ ገንዘብ ወደ ማሰባሰብ ገብተናል-የታጋች ቤተሰቦች፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ከደባርቅ ዩንቨርሲቲ ተነስተው ወደ ቤተሰቦቻቸው በመጓዝ ላይ የነበሩ ተማሪዎች እና ሌሎች መንገደኞች መታገታቸው ይታወሳል፡፡
እገታው የተፈጸመው ለአዲስ አበባ ከተማ ትንሽ ሲቀራቸው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ በታጣቂዎች እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾም ነበር፡፡
ልጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው የታገቱባቸው ሰዎች ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት ጉዳዩን መንግስት ካወቀው በኋላ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ጥረት አለማድረጉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
ለደህንነቱ በመስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ እና ቤተሰቡ የታገተበት አስተያየት ሰጪ እንዳለን ከሆነ እገታው ከተፈጸመበት ዕለት ጀምሮ ጉዳዩን መንግስት እንዳወቀው ገልጾ ነገር ግን ታጋቾቹን ለማስለቀቅ እስካሁን ምንም ጥረት እንዳላየ ተናግሯል፡፡
“መንግስት የታገተ ቤተሰቤን ያስለቅቅልኛል የሚል ዕምነት የለኝም በዚህ ምክንያት ገንዘብ ወደ ማሰባሰብ ገብተናል” ሲልም አክሏል፡፡
“ታጣቂዎቹ በየሁለት ቀኑ አንድ ጊዜ እየደወሉ 500 ሺህ ብር እንድንከፍል ያስጠነቅቁናል፣ እኔ ልጄ በአውሮፕላን ተሳፍራ እንዳትመጣ ያደረኩት አምስት ሺህ ብር ጎድሎኝ ነው፣ እጄ ላይ ምንም ገንዘብ የለኝም፣ የተባልነውን ገንዘብ በዘመድ እና ወዳጆች አማኝነት መለመን ስንጀምር ፖሊሶች መጥተው ያስቆሙናል” ብሏል ይህ አስተያየት ሰጪ፡፡
በተመሳሳይ ዕለት እና ቦታ እህቷ የታገተችባት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ በበኩሏ ታጣቂዎቹ በየዕለቱ እየደወሉ ያስፈራሩኛል ሁሌም ካንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እያዘዋወሯቸው ነው ስትል ነግራናለች፡፡
“እህቴን ጨምሮ ሶስት አውቶቡስ ላይ ተሳፍረው የነበሩ ተማሪዎች እና መንገደኞች በአደባባይ ረፋድ አራት ሰዓት ላይ ነው የታገቱት፣ ይህ ህግ አስከብራለሁ የሚል መንግስት ባለበት ነው የተፈጸመው “ ያለችን አስተያየት ሰጪዋ እስካሁን ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የተደረገ እንቅስቀሴ የለም ብላላች፡፡
ታጣቂዎቹ የታገቱትን ተማሪዎች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እያጓጓዟቸው እንደሆነ የነገረችን አስተያየት ሰጪዋ በየዕለቱ እየደወሉ ብሩን ላኪ እያሏት መሆኑንም አክላላች፡፡
እስካሁን እህቷን ሁለት ጊዜ በታጣቂዎቹ ስልክ እንዳገኘቻት የምትናገረው ይህች አስተያየት ሰጪ በድካም፣ ረሀብ እና በሚደርስባቸው ድብደባ ምክንያት ታጋቾች እየሞቱ መሆኑን እንደሰማች ተናግራለች፡፡
በታጣቂዎቹ ከታገተ ከሁለት ቀናት በኋላ መለቀቁን የሚናገረው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በበኩሉ እሱን ጨምሮ 29 ተማሪዎች መለቀቃቸውን ተናግሯል፡፡
“ታጣቂዎቹ ካገቱን በኋላ ለሶስት ቡድን ከፈሉን፣ ከዚያ የሆነ ቤት ውስጥ ግቡ አሉን ማታ ላይ የታጣቂቆቹ አለቃ ነው የተባለ ሰው መጥቶ አነጋገረን፡፡ የኦሮሚያ ነጻነት ሰራዊት መሆኑን ነገረን ከዚያ እኔን ጨምሮ 29 ልጆች ስልካችንን ጨምሮ ተወስዶብን የነበሩ ንብረቶቻችን ተመልሶልን ተለቀቅን፡፡ የታገትንበት አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች መንገድ እየመሩን ወደ ዋና መንገድ መጣን እና ወደ ቤተሰቦቻችን ሄድን” ሲልም አክሏል፡፡
ከተለቀቁ ተማሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ የሀረርጌ አካባቢ ነዋሪዎች መሆናቸውን የነገረን ይህ የደባርቅ ዩንቨርሲቲ ተማሪ ሌሎቹ ተማሪዎች እና መንገደኞች የት እንዳሉ እንደማያውቅ መንገድ ላይ ሲመጡን የጠየቃቸው የትኛውም የመንግስት አካል እንደሌለም ገልጿል፡፡
አል ዐይን አማርኛ እገታውን የፈጸመው መንግስት "ሸኔ" በሚል በሽብር የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ነው የሚለውን የዚህን ተማሪ አስተያየት ማረጋገጥ አልቻለም።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትም ይህን ክስተት በተመለከተም እስካሁን ያለው የለም።
አሜሪካ በአማራ እና ኦሮሚያ ተማሪዎችን እና ንጹሃን ዜጎችን ማገት እንዲቆም ጠየቀች
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጀይላን አብዲ የታገቱትን ተማሪዎች ለማስለቀቅ የተደረገ ጥረት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ስንጠይቃቸው “ጉዳዩ የሚመለከተው እኛን ሳይሆን የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ተቋማትን ነው፣ እነሱን ጠይቁ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙንኬሽን ጽህፈት ቤት እንዲሁም እገታው የተፈጸመበት የሰሜን ሸዋ አስተዳድር እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች በእገታው ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
ይሁን እንጅ አሻም የተባለው የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ ኃላፊን አቶ ኃይሉ አዱኛን ጠቅሶ መንግስት ታጋቾችን ለማስለቀቅ ጥረት ማድረጉን እና በዚህም ታግተው ከነበሩት 167 ተማሪዎች መካከል 160ዎቹ መለቀቃቸውን ዘግቧል።ኃላፊው ስለጉዳዩ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ከትናንት በስቲያ “በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ለገንዘብ ጥቅም ሲባል ተማሪዎችንና ሰላማውያን ዜጎችን ማገት እንዲቆምና የሕግ የበላይነት ሊከበር ይገባል” ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡