ፑቲን ሰሜን ኮሪያን የሚጎበኙበትን ቀን ክሬሚሊን ይፋ አደረገ
ያልተለመደ የተባለው የፑቲን ጉብኝት ሞስኮ ኑክሌር ከታጠቀችው ሰሜን ኮሪያ ጋር ያላት ግንኙነት እያበበ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ተብሏል
ፑቲን ከፈረንጆቹ 2000 ወዲህ ሰሜን ኮሪያን ጎብኝተው አያውቁም
የሩሲያው ፕሬዝደንት ብላድሚር ፑቲን ማክሰኞ እና ረቡዕ ሰሜን ኮሪያን እንደሚጎበኙ ክሬሚሊን ይፋ አድርጓል።
ያልተለመደ የተባለው የፑቲን ጉብኝት ሞስኮ ኑክሌር ከታጠቀችው ሰሜን ኮሪያ ጋር ያላት ግንኙነት እያበበ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ተብሏል።
የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለፑቲን የጉብኝት ግብዣ ያቀረቡላቸው ባለፈው መስከረም ወር በባቡር ወደ ሩሲያዋ ሩቅ ምስራቅ ግዛት አቅንተው በመከሩበት ወቅት ነው።
ፑቲን ከፈረንጆቹ 2000 ወዲህ ሰሜን ኮሪያን ጎብኝተው አያውቁም።
"ብላድሚር ፑቲን በኮሪያ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ግብዣ መሰረት፣ በሰሜን ኮሪያ ከ18-19 ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋል" ብሏል ክሬሚሊን።
ፑቲን ሰሜን ኮሪያን ከጎበኙ በኋላ ከ19-20 ድረስ ደግሞ ቬትናምን እንደሚጎበኙም ክሬሚሊን አክሎ ገልጿል።
ሩሲያ ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት በ60 አመታት ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይፋዊ በሆነ መንገድ በማጠናከር ላይ ነች።
በዩክሬን ከምዕራባውያን ጋር የህልውና ጦርነት እያካሄዱ እንደሆነ የሚገልጹት ፑቲን፣ ኪምን በመንከባከብ ዋሸንግተንን እና የእስያ አጋሮቿን እንዲያጠቁ እና የጦር መሳሪያ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ተብሏል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ፣ ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን በምታደርገው ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውል የጦር መሳሪያ እያቀረበች ነው ሲሉ ይከሷታል። ሰሜን ኮሪያ ግን ክሱን ምዕራባውያን የፈጠሩት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ነው ስትል በተደጋጋሚ አጣጥላዋለች።