ኪም ጆንግ ኡን ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ ጦርነት ከጀመሩ ጦራቸው ሀገራቱን “ከምድር እንዲያጠፋ” አዘዙ
የሰሜን ኮሪያው መሪ የ2024 የመጀመሪያውን ወታደራዊ ትእዛዝ አስተላልፈዋል
አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በተጠናቀቀው 2023 የመከላከያ ትብብራቸውን አጠናክረዋል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ ጦርነት ከጀመሩ ጦራቸው ሀገራቱን “ከምድር እንዲያጠፋ” ማዘዛቸው ተነግሯል።
ኪም ጆንግ ኡን በአዲሱ የፈረንጆቹ 2024 አመት መጀመሪያ የሀገሪቱንከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ሰብስበው የመጀመሪያ የተባለውን ወታደራዊ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
በዚህም ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ የትጥቅ ግጭት ከጀመሩ የሰሜን ኮሪያ ጦር ሁለቱን ሀገራት ከምድረ ገጽ እንዲያጠፋቸው አቅጣጫ መስጠታቸው ተነግሯል።
ኪም ጆንግ ኡን ባሳለፍነው ሰኞ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ፤ ጠላት ያሏቸው አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በሰሜን ኮሪያ ላይ ወታደራዊ ግጭት ከጀመሩ ጦራቸው ያለ ምንም ማመንታት ከባባድና ኃይለኛ የጦር መሳሪያዎችን ተጠቅሞ እንዲያጠፋቸው አዘዋል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ በ2023 ማጠናቀቂያ ንግግራቸው ላይ ጦርነት በማንኛውም ጊዚ ሊቀሰቀስ እንደሚችል በመግለጽ የሀገሪቱ ሰራዊት ለጢርነት የሚያደርገውን ዝግጅት እንዲያፋጥን ማዘዛቸው ይታወሳል።
ኪም አሜሪካን "የተለያዩ አይነት ወታደራዊ ትንኮሳዎች" ጀርባ እንዳለች በመግለጽ፤ ሰሜን ኮሪያን ለመከላከል የኒውክሌር ሀይልን ጨምሮ ሁሉንም አይነት የጦር መሳሪያዎች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አዘዋል።
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2023 ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ መጠናከሩን ተከትሎ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ትብብራቸውን አጠናክረዋል።