የባህር በር አልባዋ ኢትዮጵያ፤ በውጭ ሃገራት ተፈላጊ የባህር ላይ ሙያተኞችን እያፈራች ነው
በመርከቦች ላይ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት መቻሉንም የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል
የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ እስካሁን ከ1500 በላይ የባህር ላይ ሙያተኞችን ማሰልጠኑን አስታውቋል
ኢትዮጵያ በ1983 በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ከገባች በኋላ የባሕር ኃይል ጦሯ እንዲፈርስ ቢደረግም፤ ጦሩ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በድጋሚ እንዲዋቀር መንግስት አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡ ሀገሪቱ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የባሕር በር ብታጣም የመርከብ ላይ ሰራተኞችን ግን እያሰለጠነች ነው፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር ላይ ሰራተኞችን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኩል እያሰለጠነች ሲሆን እስካሁንም ከ1500 በላይ ሰልጣኞችን ሰልጥነው ወደ ተለያዩ ሀገራት መላካቸውን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ/ር) ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት በማሪታይም ኢንስቲትዩት በኩል የሰለጠኑ የባሕር ላይ ሰራተኞች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እየሆኑ ነው፡፡ አሁን ላይ በመርከቦች ላይ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት መቻሉንም ፍሬው ተገኘ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲውም፤ ከ30 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ከተቋቋመው የባሕር ኃይል ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ፍሬው ተገኘ (ዶ/ር) ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በ 1947 ዓ.ም የተቋቋመው እና በ 1983 ዓ.ም የፈረሰው የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል በደርግ ዘመን እስከ 3ሺ ጦር ነበረው፡፡ በ1983 ምጽዋ በኤርትራ ነጻ አውጭዎች ቁጥጥር ስር ከዋለችበት ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏ ቢፈርስም የባሕር ላይ ሰራተኞች ማሰልጠኛ ተቋም ግን ነበራት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በ 2010 ዓ.ም የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ከመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያን በድጋሚ ባሕር ኃይል ማቋቋም እንዳለባት ገልጸው ነበር፡፡
“በቀይ ባህር የነበረንን ተፅእኖ ፈጣሪነት ለመመለስ ተግተን መስራታችን እየደረሱብን ላሉ ጫናዎች ምክንያት ነው”-ብልፅግና ፓርቲ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር ኃይል ይቋቋማል የሚል ጉዳይ ካነሱ በኋላ “የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያ እንዴት የባሕር ኃይል ልታቋቁም ትችላለች” የሚል ሃሳብ ሲሰነዘር ነበር፡፡
‘ባሕር ወይም ውቅያኖስ ሳይኖር እንዴት ነው የባሕር ኃይልን ስለማቋቋም ልናስብ የምንችለው?’ በሚል የሚያጠይቁ አንዳንዶችም ነበሩ፡፡
በወቅቱ ከአሁን ቀደም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸው ከነበሩና ዳግም ባህር ኃይላቸውን አጠናክረው ካደራጁ ሃገራት ተሞክሮ በመውሰድ እንደሚደራጅም ነበር ሲገለጽ የነበረው፡፡
ዋናው ነገር ማሰብ፣ ፈጠራን መጠቀምና አዕምሮን ማሰራት ነው ሲሉ የሚመልሱት ዶ/ር ፍሬው ተገኝም ለባሕር ኃይል ስራ ውኃማ አካላት የሚያስፈልጉ ቢሆንም ኢትዮጵያ ደግሞ ኃይቆችና ወንዞች ስላሏት እነዚህን በመጠቀም ይህን በደንብ ዕውን ማድረግ ትችላለች ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡
የማሪታይም ስልጠና የተጀመረው ጣና ኃይቅን በመጠቀም ሲሆን እስካሁን ከ1500 በላይ ሰልጣኞች ሰልጥነው ወደተለያዩ የውጭ ሀገራት ተልከዋል፡፡
ይህ መሆኑም ታዳጊ ሀገራት የሚታወቁባቸውን ያልተማረ ሰውን ወደ ውጭ የመላክ አመለካከት ኢትዮጵያ እንድትቀይር አድርጓታል እንደ ዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ገለጻ፡፡
የባሕር ዳር ዪኒቨርሲቲ አሁን ላይ ባሕር ኃይልን በመኮንነት የሚያገለግሉ የተወሰኑ ባለሙያዎችን እያሰለጠነ ነው፡፡
ዶ/ር ፍሬው፤ ፊሊፒንስ እና ሌሎች ሀገራት አሁን ላይ የባሕር ላይ ሙያተኞችን ከኢትዮጵያ እየወሰዱ መሆኑን ገልጸው፤ ወደፊትም ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን የማሰልጠኑ ስራ ይጠናከራል ብለዋል፡፡