የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን በከፊል የመሸጡ ሂደት እንዲቆም ተደረገ
ደረቅ ወደቦችን ፕራይቬታይዝ ለማድረግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑም ይታወሳል
ሽያጩ እንዲቆም የተደረገው መንግሥት መርከቦችን ሸጦ የሚያገኘው ትርፍ መርከቦቹን በማስተዳደር ከሚያገኘው ትርፍ ሲነፃፀር አዋጪ ሆኖ ባለመገኘቱ ነው
የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን በከፊል የመሸጡ ሂደት እንዲቆም ተደረገ
መንግሥት ወደ ግል እንደሚያዛውራቸው (ፕራይቬታይዝ) ካሳወቃቸው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ፣ በከፊል እንደሚሸጥ አሳውቆ የነበረውን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ሽያጭ ሰረዘ፡፡
ሽያጩ የተሰረዘው አገልግሎቱ የሚሸጥበት ምክንያት እና ምኑን እንደሚሸጥ በዝርዝር ጥናት ሲፈተሽ አዋጪ ሆኖ ባለመገኘቱ ነው እንደ ሪፖርተር ዘገባ፡፡
በድርጅቱ ውስጥ ሊሸጡ የሚችሉት መርከቦች ናቸው ያሉት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ “መንግሥት ያሉትን 11 መርከቦች ሸጦ የሚያገኘው ትርፍና መርከቦቹን በማስተዳደር የሚያገኘው ትርፍ ሲነፃፀር አዋጪ ሆኖ ባለመገኘቱ” ሽያጩ መሰረዙን ተናግረዋል፡፡
መርከቦቹ ከሌሎች አገሮች መርከቦች ጋር ሲነፃፀሩ ያላቸው የመጫን አቅም ያን ያህል አለመሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር እንደመሆኗ ለአገሪቱ ደኅንነት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በሌሎች መርከቦች ከማስጫን በራስ መርከቦች መጠቀም የተሻለ መሆኑን መንግሥት አምኖበታልም ብለዋል፡፡
“እንደ ሉዓላዊት አገር ያለንን ጥቅም አሳልፎ መስጠት ምናልባትም የሕዝብን ጥቅም ሊጎዳ ስለሚችል፣ ለጊዜው ሽያጩ እንዲቆም ተደርጓል” ብለዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ካርጎዎችን መጫን ስለሚያስፈልግ፣ የራስ የሆነ መርከብ አለመኖር ደግሞ የአገርን ደኅንነት ጭምር ችግር ላይ ሊጥል ስለሚችል ሽያጩን በመሰረዝ ደረቅ ወደቦችን ፕራይቬታይዝ ለማድረግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሞኖፖል ተቋቁመው በመንግስት ከሚተዳደሩ የልማት ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡