ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔው ኢትዮጵያን በጠንካራ ዓለት ላይ ለማቆም በማሰብ የተወሰነ መሆኑን አውቃችሁ ተቀበሉ ሲሉ ጠይቀዋል
ክስ አቋርጦ የተወሰኑ እስረኞችን የመፍታቱ ውሳኔ የተገኘውን ዘላቂ ድል ለማዝለቅ በማሰብ የተሰጠ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል ባሉት ውሳኔ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ በአዲሱ የመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ አዲስ ህንጻ የማስመረቂያ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፡፡
ዘላቂ ድልን ማረጋገጥ ማሸነፍ ብቻም ሳይሆን ይቅር ብሎ ምህረት ማድረግን ይሻል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁጣው ጭር ሲል ከማይወድና የት እንዳለ ከማይታወቅ ቡድን እና በዜናው ድንገተኛነት ከደነገጠ ጠላትን አምርሮ ከሚጠላ “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ” መሰማቱን ተናግረዋል፡፡
ይህን የሚረዳው መንግስት “እኛንም መጀመሪያ አስደንግጦን ነበር” ስላሉት ውሳኔ ለማስረዳት ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
“እየመረረን የዋጥነው ነው” ሲሉም ነው ስለ ውሳኔው ያስቀመጡት፡፡ ሆኖም ውሳኔው ለኢትዮጵያ የሚበጅና ጠላትን የሚቀንስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን በጠንካራ ዓለት ላይ ለማቆም በማሰብ የተወሰነ መሆኑን አውቃችሁ ለሃገር አሸናፊነት ስትሉ ውሳኔውን እንድትቀበሉ እጠይቃለሁም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ክስ ተቋርጦ የተፈቱት አካላት ልክ እንደካሁን ቀደሙ ሁሉ የመንግስት ስልጣን ይዘው የሚወስኑ እንዳይደሉም ተናግረዋል፡፡
አንዳንዶቹን በታሪካቸው አግዝፈን ብናያቸውም በውሳኔዎች የቀጥታ ተሳትፎ የሌላቸው አዛውንቶች ናቸው ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
አዛውንቶች ወደ ቤተክርስቲያን እንዲሄዱ እንጂ እስር ቤት እንዳይቆዩ በማሰብ ወስነናልም ብለዋል፡፡
ልጆቻችንን የሚያኮራ ነው ያሉት ውሳኔ በማሸነፋችን ያገኘነው ጸጋ ነው ሲሉም ተናግረዋል፤ ለዚህ ፈጣሪን ማመስገን እንደሚገባ እና ጠላት አሸንፎ ቢሆን እንደማያደርገው በመጠቆም፡፡
ይቅር ያልነው እየቻልን መሆኑ ሊታወቅ ይገባልም ብለዋል፡፡
ከጀርባችሁ ያለውን ህዝብ በማክበር የተወሰነ መሆኑን አውቃችሁ በአግባቡ ተጠቀሙበት ሲሉም ከእስር ለተፈቱ አካላት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በውሳኔው ያዘኑና የተቆጡ ኢትዮጵያውያን ውሳኔው ሃገር ማጽናትን በማሰብ የተወሰነ መሆኑን አውቀው ቢጎረብጥም ደጋግመው እንዲያስቡበት ጠይቀዋል፡፡
መንግስት በጃዋር መሃመድ እና በእስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ የተከሰሱትን ጨምሮ በእነ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው ውስጥ የጤና እና የዕድሜ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የስድስት ግለሰቦች ክስ እንዲነሳ ማድረጉን ማስታወቁ የሚታወስ ነው።