ዛሬ በሳንቲያጎ በርናቤው ለበቀል አንጫወትም ያሉት ፔፕ ጋርዲዮላ፥ የፍጻሜ ተፋላሚው የሚለየው በኢትሃዱ የመልስ ጨዋታ ነው ብለዋል
የሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ዛሬ ሲጀመር ሪያል ማድሪድ በሳንቲያጎ በርናቤው ማንቸስተር ሲቲን ይገጥማል።
የጣሊያኖቹ ኤሲ ሚላን እና ኢንተር ሚላን ደግሞ በነገው እለት ይፋለማሉ።
ቼልሲን 4 ለ 0 አሸንፎ ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለው ሪያል ማድሪድ ባለፈው አመት በአስደናቂ ሁኔታ ሲቲን ከሻምፒዮንስ ሊጉ ውጭ ማድረጉ ይታወሳል።
በኢትሃድ 4 ለ 3 አሸንፈው ወደ በርናባው ያመራው የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን በሪያድ ማህሬዝ ጎል የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ቢያሰፉም ተቀይሮ የገባው ሮድሪጌዝ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ሁለት ጎሎችን ኣምስቆጠሩ የሚታወስ ነው።
ይህን ተከትሎ በተሰጠው ተጨማሪ የጨዋታ ጊዜም ካሪም ቤንዜማ በ95ናው ደቂቃ ጎል አስቆጥሮ የካርሎ አንቸሎቴ ቡድን የዋንጫ ተፋላሚ እንዲሆን ማስቻሉ አይዘነጋም።
ፔፕ ጋርዲዮላ ዛሬ ወደ ሳንቲያጎ በርናባው የምንገባው ያለፈውን አመት ውጤት ለመበቀል አይደለም፤ የፍጻሜ ተፋላሚነታችን የሚረጋገጠው በኢትሃድ በሚደረገው የመልስ ጨዋታ ነው ብለዋል።
ባየርሙኒክን በደርሶ መልሶ 4 ለ 1 አሸንፎ ለግማሽ ፍጻሜው የደረሰው ሲቲ ለሶስት ዋንጫዎች እየተፎካከረ ነው፤ የፕሪሚየር ሊግ፣ ኤፍ ኤ ካፕ እና ሻምፒዮንስ ሊግ።
ሪያል ማድሪድ በበኩሉ የላሊጋ ዋንጫው በባርሴሎና መነሳቱ አይቀሬ መሆኑን በማመን ሙሉ ትኩረቱን ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ማድረጉ ነው የሚነገረው።
ባለፈው አመት የእንግሊዙን ሊቨርፑል በመርታት የአውሮፓ ትልቁን ዋንጫ ያነሳው የስፔኑ ክለብ ያለፈውን አመት ድሉን ያሳካው ይሆን? የሚለው ተጠባቂ ሆኗል።
በ2021 በቼልሲ ተሸንፎ ዋንጫውን ያጣው ማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ግን ዘንድሮ ዋንጫውን የማንሳት እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።