የሻምፒዮንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ 11 ተጫዋቾች ዝርዝርም ይፋ ሆኗል
የሪያል ማድሪድ እና የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ካሪም ቤንዜማ የዓመቱ ምርጥ የሻምፒዮንስ ሊግ ተጫዋች በሚል ተመረጠ፡፡
ፈረንሳዊው የ 34 ዓመት አጥቂ በ 12 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች 15 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ተጫዋቹ የሻምፒንስ ሊግ ዋንጫን ለአምስተኛ ጊዜ አሸንፏል፡፡ ቤንዜማ የባለን ደዖር አሸናፊ የመሆን ዕድል እንዳለውም እየተገለጸ ነው፡፡
ሪያል ማድሪድ እና ሊቨርፑል ባደረጉት የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ላይ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ቪኒሺየስ ጁኒየርም የውድድሩ ምርጥ ወጣት ተጫዋች በሚል ተመርጧል፡፡ ብራዚላዊው ቪኒሺየስ ጁኒየር በ 2021/ 2022 የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ዓመት አራት ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን ስድስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችንም አቀብሏል፡፡
የሪያል ማድሪዶቹ ካሪም ቤንዜማ፣ ቪኒሺየስ ጁኒየር ፣ ሉካ ሞድሪች እና ቲቡአ ኩርትዋ የዓመቱ የሻምፒዮንስ ሊግ ምርጥ ስብስብ ውስጥ ተካተዋል፡፡ የፍጻሜ ተፋላሚ የነበረው ሊቨርፑል አራት ተጫዋቾችም የዓመቱ የሻምፒዮንስ ሊግ ምርጥ ስብስብ ውስጥ ተካተዋል፡፡ ተጫዋቾቹም አሌክሳንደር አርኖልድ፣ ቨርጂል ቫንዳይክ፣ ኤንዲ ሮበርትሰንና ፋቢንሆ ናቸው፡፡
ቀሪዎቹ ተጫዋቾች ደግሞ የፓሪስ ሴንት ጀርሚኑ አጥቂ ኪሊያን ምባፔ፣ የማንቸስተር ሲቲው አማካይ ኬቪን ደብሮይነ እና የቸልሲው ተከላካይ አንቶኒ ሩዲገር ናቸው፡፡