የዩሮፓ ሊግ የመጨረሻ 16 ክለቦች ድልድል ዛሬ ይፋ ሆኗል
የዩሮፓ ሊግ የመጨረሻ 16 ክለቦች ድልድል ዛሬ ይፋ ሆኗል
ማንችስተር ዩናይትድ ክለብ ብሩዥን በሰፊ ልዩነት አሸንፎ ነው ቀጣዩ ዙር ማለፉን ያረጋገጠው፡፡
ትናንት ምሽት በሁለቱ ክለቦች መካከል በኦልድ ትራፎርድ የተደረገው የዩሮፓ ሊግ የመልስ ጨዋታ በዩናይትድ 5 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ወደጎል የምታመራ ኳስን በእጁ የመለሳት የብሩዥ ተከላካይ ዴሊ በ22ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ወጥቶ ማንችስተር ያገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት በማስቆጠር የጨዋታው ኮከብ ብሩኖ ፈርናንዴዝ የዩናይትድን ጎል ሲያስጀምር እስከ ዓመቱ ፍጻሜ ክለቡን በውሰት የተቀላቀለው ኢጋሎ 2ኛውን፣ ማክቶምኔ 3ኛውን እና ፍሬድ ቀሪዎቹን 2 ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡
“ይህ ለኔ ትልቅ አጋጣሚ ነው፤ ይሄን ጊዜ በጉጉት ስጠብቀው ነበር” ያለው ኢጋሎ “ከልጅነቴ ጀምሮ ለምደግፈው ክለብ ጎል የማግባት ስራዬን ጀምሪያለሁ” ሲል ተናግሯል፡፡
ኢጋሎ በዩናይትድ መለያ ያስቆጠራትን የመጀመሪያ ጎሉን፣ የወንድሟ ወደምትደግፈው ክለብ የመዛወር ህልም እውን ከመሆኑ ከሰባት ሳምንታት በፊት በካናዳ ድንገት ህይወቷላለፈው የ42 ዓመት እህቱ መታሰቢያ አድርጓል፡፡
አርሰናል ደግሞ በሜዳው በኦሎምፒያኮስ ተሸንፎ ከዩሮፓ ሊግ ተሰናብቷል፡፡
በኤሚሬትስ በተደረገው የመልስ ጨዋታ ኦሎምፕያኮስ መደበኛውን የጨዋታ ጊዜ ሲሴ በ53ኛ ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል አንድ ለባዶ እየመራ ነው ያጠናቀቀው፡፡
አርሰናል በመጀመሪያው ዙር በኦሎምፒያኮስ ሜዳ 1 ለ 0 አሸንፎ የተመለሰ እንደመሆኑ፣ በ90 ደቂቃዎች ድምር ውጤታቸው አንድ እኩል በመሆኑ በተጨመረ 30 ደቂቃ ውስጥ ለመድፈኞቹ አምበሉ ኦባምያንግ ያስቆጠራት ጎል አርሰናልን ጮቤ ብታስረግጥም ኤል-አራቢ በ119ኛው ደቂቃ ለጎብኚዎቹ ያስቆጠራት ጎል፣ ከሜዳ ውጭ ብዙ ባስቆጠረ፣ ኦሎምፒያኮስን ወደ 16ቱ ስትቀላቅል የአርሰናልን የዩሮፓ ሊግ ጉዞ ገትታለች፡፡
ወትሮውን በአስቸጋሪ ጊዜያት አርሰናልን በመታደግ የሚታወቀው ኦባምያንግ የጨዋታው ማብቂያ ፊሽካ ከመነፋቱ በፊት ባለቀ የባከነ ሰዓት ያገኛትን ግሩም ነጻ ኳስ ኢላማውን ጠብቆ ወደ ጎል መምታት አለመቻሉ የክለቡን ዋጋ አስከፍሏል፡፡
በጎሏ አለመቆጠር የተጋጣሚ ተጫዋቾችም ጭምር ሲደናገጡ ታይተዋል፡፡ ኦባምያንግም እንዴት እንዳላስቆጠርኩ እኔም አልገባኝም ሲል ንዴቱን ገልጿል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ በዝግ ሜዳ በተደረገ ጨዋታ ኢንተርሚላን ሉዶጎሬትስን 2 ለ1 ሲያሸንፍ በድምር ውጤት 4 ለ 1 ወደ ቀጣዩ ምእራፍ ተሻግሯል፡፡
የዩሮፓ ሊግ የመጨረሻ 16 ክለቦች ድልድልም ዛሬ ይፋ ሆኗል፡፡ በዚህም መሰረት ማንችስተር ዩናይትድ ከኦስትሪያ ሊግ መሪው በምህጻረ ቃሉ-ላስክ ጋር ሲደለደል፣ ዎልቭስ ከ ኦሎምፒያኮስ፣ ሬንጀርስ ከ ባየር ሌቨርኩሰን፣ ዎልፍስበርግ ከ ሻክታር ዶኔስክ፣ ኢንተር ሚላን ከ ጌታፌ እና ሲቪያ ከ ሮማ ተደልድለዋል፡፡ ዛሬ የሚጋጠሙት የኢንትራ ፍራንክፈርት እና የአርቢ ሳልዝበርግ አሸናፊ ደግሞ ከባዘል ይገናኛል፡፡
ምንጭ፡-ቢቢሲ