ሜሲ የፊታችን አርብ ክለቡ የሜክሲኮውን ክሩዝ አዙል ሲገጥም ይሰለፋል
ሊዮኔል ሜሲ የአሜሪካውን ኢንተር ሚያሚ በይፋ ከተቀላቀለ በኋላ የስታዲየም መግቢያ ትኬት ዋጋ መናሩ ተነግሯል።
በኦንላይን የሚሸጡ ትኬቶችን በድጋሚ የሚሸጥ ኩባንያን ጠቅሶ ሲኤንኤን እንዳስነበበው፥ ሜሲ ለክለቡ ኢንተር ሚያሚ የሚያደርገውን የመጀመሪያ ጨዋታ ለመመልከት የአንደኛ ደረጃ (ቪአይፒ) አንድ ትኬት 110 ሺህ ዶላር ተሽጧል።
ይህም በተለያዩ ሀገራት ቤት መግዛት የሚያስችል መሆኑን ነው ዘገባውን የሚጠቅሰው።
በአሜሪካ የእግር ኳስ ታሪክ ለስታዲየም መግቢያ የተከፈለ ከፍተኛው የትኬት ዋጋ ሆኖ የተመዘገበው ሽያጭ አርጀንቲናዊውን ኮከብ በአሜሪካ ለማየት ያለውን ጉጉት ያሳያል ተብሏል።
አድናቂዎቹ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ሜሲን ለመመልከት ሺህ ኪሎሜትሮችን አቆራርጠው ፍሎሪዳ መግባት መጀመራቸውም እየተነገረ ነው።
እስካሁን ባለው መረጃ የሜሲን የመጀመሪያ የኢንተር ሚያሚ ጨዋታ ለመመልከት የስታዲየም መግቢያ ትኬት ዋጋው 476 ዶላር መድረሱ ተገልጿል።
ይህም እስካሁን ከነበረው የ700 ፐርሰንት ጭማሪ እንዳለው ያሳያል ነው የተባለው።
ሜሲ ኢንተር ሚያሚ እንደሚቀላቀል ጭምጭምታ ከተሰማ በኋላ ክለቡ ነሃሴ 20 ላይ ከአሜሪካው ቻርሎቴ ጋር ለሚያደገው ጨዋታ የትኬት ዋጋ በ900 ፐርሰንት መጨመሩንም ነው ሲኤንኤን ያወሳው።
የሰባት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ባለፈው ቅዳሜ በአመት 60 ሚሊየን ዶላር ክፍያ የእነዴቪድ ቤካም ክለብን ኢንተር ሚያሚ መቀላቀሉ ይታወሳል።
ኢንተር ሚያሚ የሜክሲኮውን ክሩዝ አዙል የፊታችን አርብ ሲገጥምም የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።