ኢንተር ሚያሚ በሚቀጥለው ቅዳሜ የሜክሲኮውን ክሩዝ አዙልን ሲያስተናግድ ሜሲ ለክለቡ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል
አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮነል ሜሲ በአሜሪካው ኢንተር ሚያሚ በፈረንጆቹ እስከ 2025 የሚያቆየውን ፊርማ ማጠናቀቁን ሜጀር ሶከር ሊግ አስታውቋል።
የሰባት ጊዜ ባላንዶር አሸናፊው ሜሲ በሚቀጥሉት ቀናት ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሏል።
"ይህ ትልቅ እድል ነው እናም ይህን ቆንጆ ፕሮጀክት አንድላይ ሆነን እንገነባለን"ብሏል ሊዮነል ሜሲ።
ሜሲ "ሀሳቡ እኛው ያስቀመጥናቸውን እቅዶች ከግብ ማድረስ ነው፣ ይህ እንዲሳካ ለማድረግ ከእዚህ ከአዲሱ ቤቴ እሰራለሁ" ሲል ተናግሯል።
ኢንተር ሚያሚ በሚቀጥለው ቅዳሜ የሜክሲኮውን ክሩዝ አዙልን ሲያስተናግድ ሜሲ ለክለቡ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።
በቡድኑ የባለቤትነት ድርሻ ያለው ዴቪድ ቤካም "ከአለም ምርጥ የሚባሉ ተጫዋቾችን ለማምጣት ሳልም ነበር" ብሏል። "ዛሬ ያ ህልም እውን ሆኖል። ሊዮነል ሚሴ ወደ ክለባችን በመምጣቱ ኩራት ይሰማኛል። ሜሲን እና ቤተሰቦቹን ወደ ኢንተር ሚያሚ ማህበረሰብ እንኳን ደህና መጣችሁ" በማለት ቤካም ደስታውን ገልጿል።
የአለምዋንጫ አሸናፊው ሊዮነል ሜሲ አሜሪካ መግባት በአሜሪካ ያለውን እግርኳስ ያነቃቃል ተብሏል።
ሜሲ በዛሬው እለት ዲአርቪ ፒኤንኬ ስቴድየም በሚኖረው የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ራሱን ከደጋፊዎች ጋር እንደሚያስተዋውቅ ይጠበቃል።
ሜሲ ከክለቡ ሚያሚ ጋር በመሆን ሰኞ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣልም ተብሏል።
ሊዮነል ሚሴ በፊፋ2023 በኳታር የተካሄደውን የአለም ዋንጫ ሀገሩ አርጀንቲና እንድታነሳ ከፍተኛውን ድርሻ በመወጣቱ አድናቆት ማትረፉ ይታወሳል።