ሞሮኮ ለ2030 የአለም ዋንጫ ዝግጅት መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት 1 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አገኘች
ስፔን ፣ ፖርቹጋል እና ሞሮኮ በጋራ ለሚያዘጋጁት የአለም ዋንጫ አፍሪካዊቷ ሀገር መሰረተ ልማቶችን ለማደስ እና ስታድየሞችን ለመገንባት ነው የገንዘብ ድጋፉ የተደረገላት

ከ2010 የደቡብ አፍሪካ የአለም ዋንጫ ቀጥሎ አፍሪካዊት ሀገር በአለም ዋንጫ አዘጋጅነት ስትሳተፍ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው
የአፍሪካ ልማት ባንክ ሞሮኮ ከስፔን እና ፖርቹጋል ጋር በመሆን በ2030 ለምታዘጋጀው የአለም ዋንጫ ጨዋታ የሚሆን መሰረተልማት ግንባታ የአንድ ቢሊየን ዶላር የብድር ስምምነት አጽድቋል፡፡
ባንኩ 370 ሚሊየን ዶላር በመጀመርያው ዙር ለሀገሪቱ የሚሰጥ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ ከ680 ሚሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ለመልቀቅ ቃል ገብቷል፡፡
ሞሮኮ ከ2010 የደቡብ አፍሪካ የአለም ዋንጫ ቀጥላ ሁለተኛዋ አፍሪካዊት ሀገር በመሆን ከስፔን እና ፖርቹጋል ጋር ተወዳጁን የአለም የእግር ኳስ ትዕይንት ለማዘጋጀት በምታደርገው ጥረት የገንዘብ ድጋፉ ተጨማሪ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው የተባለው።
የባንኩ አጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ አጠቃላይ 37 ፕሮጀክቶችን በ3.6 ቢሊዮን ዶላር ለመግንባት ላቀደችው ሀገር ያጋጠማትን የበጀት ጉድለት የሚያግዝ ነው፡፡
ሀገሪቱ የገንዘብ ድጋፉን ስታድየሞችን ፣ የአየር ፣ የባቡር እና የመንገድ ትራንስፖርቶችን ለማሟላት የምታውለው ይሆናል፡፡
ባለፈው አመት በመንግስት በተገለፀው መሰረት በካዛብላንካ አቅራቢያ በምትገኘው ቤንስሊማኔ ዘመናዊ ስታዲየም ለመገንባት እና 6 ነባር ስታዲየሞችን የማደስ አላማ አላት።
በተጨማሪም የሞሮኮ ኢኮኖሚ አስተዳደርን ማሳደግ፣ የውሃ አቅርቦት ስርዓትን ማሻሻል እና በናዶር ዌስት ሜድ ወደብ ላይ የኢንዱስትሪ ዞን መገንባት ላይ እንደሚያተኩር የአፍሪካ ልማት ባንክ መግለጫ አመላክቷል፡፡
የልማት ባንኩ ፕሬዝዳንት አኪንዋሚ አዴሲና እና የሞሮኮ ጠቅላይ ሚኒስትር አዚዝ አካንኑች ባደረጉት ወይይት የገንዘብ ድጋፉ ከመሰረተ ልማት ግንባታ ባሻገር የወጣቶች ሥራ ፈጠራ እና ክህሎት ማዳበሪያን የመሳሰሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ እንደሚውልም ነው የተነገረው፡፡
አዴሲና ለሞሮኮ ንጉስ መሀመድ ስድስተኛ ለአፍሪካ ልማት ባንክ ያላሰለሰ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረምን በራባት በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ በማስቻል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የ2030ው የአለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሶስት ሀገራት አዘጋጅነት የሚካሄድ ይሆናል፡፡